
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች በአማራ ክልል በገቢ አሠባሠብ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ እያደረጉ ነው።
የልምድ ልውውጡ የአማራ እና የአፋል ክልል ገቢዎች ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ነው በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው ( ዶ.ር) ሁለቱ ክልሎች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በጅኦግራፊ ተሳስረው ፈተናዎችን በጽናት አልፈዋል ብለዋል።
ሁለቱ ክልሎች ወድማማችነትን ለረጅም ጊዜያት ያፀኑ እና የተሳሳረ ግንኙነታቸውን ለሌሎችም ያስተማሩ የታሪክ ባለቤቶች እንደኾኑ ጠቁመዋል። ሁለቱ ክልሎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸውም ነው ያሉት።
መርሐ ግብሩ የገቢ አሠባሠብ ልምድ ልውውጥ ለማድረግ ታልሞ መዘጋጀቱንም አንስተዋል። በሁሉም ዘርፎች ያሉ የገቢ አሠባሠብ ልምድን ለማጋራት መዘጋጀታቸውንም ነው የገለጹት።
በክልሉ የገጠሙ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር የገቢ አሠባሠብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ባለፉት ሦሥት ዓመታት በተለይም በ2016 በጀት ዓመት 40 ቢሊዮን እንዲሁም በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ከ61 ቢሊዮን በላይ ብር ገቢ መሠብሠቡን ተናግረዋል።
ሰላምን እያረጋገጡ ልማት መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው በፈተና ውስጥ ዕቅድን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም ከ100 ቢሊዮን በላይ ብር ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በቁጭት ሥራዎች እየተሠሩ ነውም ብለዋል። የሁለቱ ክልሎች ግንኙነት እና ወንድማማችነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በልምድ ልውውጡ በአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ሃጂ አወል አብዱ አወል የሚመራ ልዑክ እየተሳተፈ ይገኛል።
ዘጋቢ ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
