በአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ የሊግ ‘ኤ’ ምድብ ሦሥት ጨዋታ ስፔን ክሮኤሺያን 4 ለ 1 በኾነ ሰፊ ውጤት ያሸነፈችበትን ሁለተኛ ድሏን
አስመዝግባለች።
ምድቡንም በ6 ነጥብ እየመራች ነው። በጨዋታው ላሚን ያማል በ2ኛው እና በ63ኛው ደቂቃ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፣ ማርክ ፑቢል በ31ኛው እንዲሁም ኒኮ ዊሊያምስ በ89ኛው ደቂቃ የቀሩትን ግቦች አስቆጥረዋል። ለክሮሺያ ብቸኛዋን ግብ ቤልዮ በ28ኛው ደቂቃ ላይ አስመዝግቧል።
በዚሁ ምድብ እንግሊዝ ቼክ ሪፐብሊክን 2 ለ 0 በኾነ ውጤት አሸንፋለች።
የእንግሊዝ እና ቼክ ሪፐብሊክ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በዜሮ ውጤት ነው የተጠናቀቀው። የቼክ ሪፐብሊኩ ሹልች በ25ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ውጭ መኾኑ ለእንግሊዝ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላታል። ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረም እንግሊዝ በ47ኛው ደቂቃ በአንቶኒ ጎርደን እንዲሁም በ69ኛው ደቂቃ በሃሪ ኬን አማካይነት ባስቆጠረቻቸው ግቦች ማሸነፍ ችላለች። ይህም ባለፈው ሽንፈት የገጠማት እንግሊዝ ወደአሸናፊነት እንድትመለስ አስችሏታል። ከምድቡም 3 ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ክሮሽያን በልጣ ሁለተኛ መኾንም ችላለች።
በሌሎች የአውሮፓ ኒሽንስ ሊግ በተደረጉ የቡድን ጨዋታዎች በምድብ አንድ ስዊዘርላንድ ስኮትላንድን 3 ለ 0፣ አልባንያ ሳን ማሪኖን 3 ለ 0 እንዲሁም ስሎቬንያ ሰሜን ማቄዶንያን 2 ለ 0 በኾነ ውጤት አሸንፈዋል፤ በፊንላንድ እና ቤላሩስ መካከል የተደረገው ጨዋታ ደግሞ ያለ ምንም ግብ በዜሮ ለ ዜሮ አቻ ውጤት ተጠናቅቋል።
በምድብ ሦሥት ስሎቫኪያ ካዛኪስታንን 2 ለ 1 አሸንፈዋል፤ በሌላ በኩል ሞልዶቫ ከፋሮ ደሴቶች ጋር አንድ ለአንድ በኾነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
በምድብ አራት ደግሞ አይስላንድ ሉክሰምበርግን 3 ለ 0 በኾነ ውጤት ስታሸንፍ፣ በቡልጋሪያ እና ኢስቶንያ መካከል የተደረገው ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በዜሮ ለ ዜሮ አቻ ውጤት ተጠናቅቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



