የሳዑዲ ዓረቢያው ክለብ አል-ናስር ሴኔጋላዊውን ኮከብ ሳዲዮ ማኔን በያዝነው የውድድር ዓመት መጨረሻ ኮንትራቱ ሲጠናቀቅ ለመልቀቅ መወሰኑ ተሰምቷል።
የሳዑዲ መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ ጎል ዶት ኮም እንደዘገበው የማኔ ወኪል ተጫዋቹ ለተጨማሪ አንድ የውድድር ዓመት በክለቡ እንዲቆይ የደመወዙን 60 በመቶ ለመቀነስ ፈቃደኛ መኾኑን ቢያሳውቅም አል-ናስር ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
በዚህም መሠረት ማኔ በመጪው የጥር የዝውውር መስኮት ከፈለገው ክለብ ጋር ቅድመ-ስምምነት ፈርሞ በክረምቱ በነፃ ዝውውር መልቀቅ ይችላል ስለማለቱ ነው የተገለጸው።
እ.ኤ.አ. በ2023 ክረምት ከባየርን ሙኒክ አል-ናስርን የተቀላቀለው የ34 ዓመቱ አጥቂ ባለፉት ሦሥት ዓመት ተኩል ቆይታው በ144 ጨዋታዎች ተሰልፎ 54 ግቦችን ሲያስቆጥር 43 ግብ የኾኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



