ኬንያውያኑ አትሌቶች በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት እገዳ ተላልፎባቸዋል፡፡
ኬንያውያኖቹ የማራቶን ሯጮች ፔሪስ ጀፕቸርቸር እና ሮናልድ ኮሪር ደግሞ ከ ሦሥት እስከ ስድስት ዓመት እገዳ እንደተጣለባቸው የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ይፋ አድርጓል፡፡
የወቅቱ የዓለም ሻምፒዮን እና የቀድሞ የኦሊምፒክ አሸናፊ የኾነችው ፔሬስ ጄፕቺርቺር ኢፒኦ (EPO) የተሰኘውን አበረታች ንጥረ ነገር በመጠቀሟ ምክንያት የሦሥት ዓመት እገዳ ተጥሎባታል።
የኒውዮርክ፣ የቦስተን፣ የለንደን እንዲሁም በዘንድሮው ነሐሴ ወር የተካሄደውን የሲድኒ ማራቶን ጨምሮ የበርካታ ታላላቅ የዓለም ማራቶኖች አሸናፊ የኾነችው የ33 ዓመቷ አትሌት፣ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ አንቀጽ 2 ነጥብ 1ን ማለትም አትሌቷ በሰጠችው ናሙና ውስጥ የተከለከለ ንጥረ ነገር መገኘቱ እና አንቀጽ 2 ነጥብ 2ን የተከለከለ ንጥረ ነገር ወይም ዘዴ መጠቀም ወይም ለመጠቀም መሞከር የሚሉ ደንቦችን መጣሷን አትሌቷ አምናለች።
ጄፕቺርቺር በነሐሴ ወር የሲድኒ ማራቶንን ከማሸነፏ በፊት በኬንያ ከውድድር ውጪ በተወሰደባት ናሙና፣ መስከረም 17/2026 ኢፒኦ (EPO) መገኘቱ በመረጋገጡ ጥቅምት 20/2026 በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ጊዜያዊ እገዳ ተጥሎባት ነበር።
አትሌቷ በዕለቱ በተደረገላት ቃለ መጠይቅ ኢ.ፒ.ኦ አለመጠቀሟን እና ውጤቱ እንዴት እንደተከሰተ እንደማታውቅ ተናግራ ነበር።
ኾኖም የቀድሞዋ የግማሽ ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት በኋላ ላይ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ መጣሷን እና ቅጣቱን እንደምትቀበል የሚገልጽ ሰነድ በመፈረሟ የሲድኒ ማራቶን ድሏን ጨምሮ ከሐምሌ 17/2026 ጀምሮ ያስመዘገበቻቸው የውድድር ውጤቶች በሙሉ እንዲሰረዙ ተወስኗል፡፡
በተመሳሳይ የ2026 የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ላይ በግማሽ ማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረችው ቬሮኒካ ሎሌዎ በተመሳሳይ ኢፒኦ የተሰኘው አበረታች ንጥረ ነገር በናሙናዋ ውስጥ መገኘቱን እና መጠቀሟ በአንቀጽ 2 ነጥበብ 1 እና 2 ነጥብ 2 መጣሷን በማመኗ የሦሥት ዓመት እገዳ ተጥሎባታል።
በሌላ በኩል በ2023 የበርሊን ማራቶን አራተኛ ኾኖ ያጠናቀቀው የ35 ዓመቱ ሮናልድ ኮሪር፣ በአትሌት ላይ በታዩ ያልተለመዱ ለውጦች ዙሪያ አጥጋቢ ማብራሪያ ባለመስጠቱ አንቀጽ 2 ነጥብ 2ን በመጣስ የስድስት ዓመት እገዳ ተላልፎበታል።
እ.ኤ.አ. ከ2023 እስከ 2025 ከአትሌት ኮሪር በተወሰዱ 20 የደም ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ከሃምቡርግ እና ከኦሳካ ማራቶን ውድድሮች በፊት በነበሩ ወቅቶች አበረታች ቅመሞችን መጠቀሙን የሚጠቁሙ ያልተለመዱ ውጤቶች ተገኝተውበታል።
በዚህም መሠረት የአትሌቲክስ ኢንቴግሪቲ ዩኒት ግንቦት 20/2026 ጉዳዩን በይፋ ቢያሳውቀውም አትሌቱ ቃለ መጠይቅ ካደረገ በኋላ ለተገኙት ያልተለመዱ ውጤቶች በጽሑፍ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሁለት ጊዜ ተጠይቆ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።
በዚህም ምክንያት የመጀመሪያው ናሙና ከተገኘበት ከጥር 19/2024 ጀምሮ የተሳተፈባቸው የውድድር ውጤቶች በሙሉ እንዲሰረዙ ተወስኗል።
ኢፒኦ (EPO) በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (WADA) የ2026 የተከለከሉ ንጥረ ነገሮች ዝርዝር ውስጥ በምድብ S2 (Peptide Hormones, Growth Factors, Related Substances, and Mimetics) ስር የሚገኝ እና በማንኛውም ጊዜ ፈጽሞ የተከለከለ ንጥረ ነገር ነው።
ጄፕቺርቺርም ኾነች ሎሌዎ የአራት ዓመት እገዳ ተጠብቆባቸው የነበረ ቢኾንም ጥፋታቸውን አስቀድመው በማመናቸው እና ቅጣቱን በመቀበላቸው በሕጉ መሠረት የአንድ ዓመት ቅናሽ ተደርጎላቸዋል።
የAIU ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ብሬት ክሎዚየር ይሄንን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት አስተያየት “የኬንያ መንግሥት ወቅታዊውን ሁኔታ ተገንዝቦ የኬንያን የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ የበለጠ ለማጠናከር እና በሀገሪቱ ውስጥ አበረታች ቅመሞችን የሚያሰራጩ የወንጀል መረቦችን ለመቆጣጠር ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
በሚቀጥሉት ወራት ከኬንያ መንግሥት ጋር በእነዚህ ጉዳዮች ውይይት ይኖረናልም ብለዋል። ባጠቃላይ ኬንያ እስካሁን ድረስ 148 አትሌቶቿ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም ተቀጥተዋል፡፡
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



