‎🏟️ ከዓመታት የሜዳ አልባነት ስደት በኋላ በባሕር ዳር ስታዲየም የተመለሰው ክብር።

0
77

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ደረጃውን በጠበቀ የመጫወቻ ሜዳ ማጣት ምክንያት ከሀገር ውጭ ውድድሩን ሲያካሂድ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ስታዲዬሞች የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) መስፈርት ሳያሟሉ ለዓመታት ዘልቀዋል። አሁን ግን የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የካፍ መስፈርትን በማሟላቱ ጨዋታ እንዲያደርግ ፈቃድ ተሰጥቶታል። ስታዲዬሙ ከዓመታት ቆይታ በኋላ መስከረም 19/2019 ዓ.ም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ ውድድር ይመለሳል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከሴኔጋል አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ለስታዲየሙ ወደ ውድድር መመለስ መነሻ ኾኗል።

የስታዲየሙ ሥራ አሥኪያጅ ምስክር ሰውነት የካፍ የፍተሻ ቡድን በተደጋጋሚ የሰጣቸው የማስተካከያ ሥራዎች ተጠናቅቀው ጨዋታ ለማስተናገድ ፈቃድ ማግኘቱን በትልቅ ስኬትነት አንስተዋል።

የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ስታዲየሙን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የሰጣቸውን አስተያየቶች መሠረት በማድረግ ሰፊ የማስተካከያ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

ስታዲየሙ አስፈላጊ ሥራዎች ተሟልተው ፈቃድ በማግኘቱም ወደ ውድድር መመለሱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደሚያስገኝ ጠቁመዋል።

ስፖርታዊ ክንውኑ በክልሉ የስፖርት ቱሪዝምን በከፍተኛ ደረጃ ከማነቃቃቱም ባሻገር፣ የሆቴሎችን አቅም በማሳደግ ለከተማዋም ኾነ ለክልሉ የጎላ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንደሚያስገኝ ተገልጿል።

መላው የስፖርት አፍቃሪ በዕለቱ በስታዲየም ተገኝቶ ለብሔራዊ ቡድኑ ደማቅ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ይህንንም ሲያከናውን ሕግ እና ሥርዓትን በማክበር፣ የጸጥታ አካላትን ትዕዛዝ በመቀበል ጨዋነቱን እንዲያሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

#AMECO #Ethiopia_Senegal #BahirDar stadium🇪🇹

#አሚኮ_ባሕር_ዳር #መስከረም_14_2019_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here