ዓለም የመጭውን ዕለተ እሑድ የበርሊን ማራቶን በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል። ውድድሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጠበቅ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ይመዘገባል ተብሎ በመጠበቁ ነው። ሌላው ደግሞ የረጅም ርቀት ሩጫ ንጉሡ ቀነኒሳ በቀለ ከ2019 በኋላ ወደ በርሊን ማራቶን መመለሱ ነው።
የ2026 የበርሊን ማራቶን በመጭው እሑድ መስከረም 17/2019 ዓ.ም የሚካሄድ ሲኾን የሴቶች የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ትዕግሥት አሰፋ ለሌላ ታሪካዊ ክብር ወደ መድረኩ ትመለሳለች።
ለበርሊን ጎዳናዎች አዲስ ያልኾነችው ትዕግሥት አሰፋ ከዚህ ቀደም ባደረገቻቸው ሁለት ውድድሮች ድንቅ ታሪክ ጽፋለች።
በ2022 በመጀመሪያ ተሳትፎዋ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ በመግባት ስታሸንፍ፣ በ2023 በድጋሚ ተመልሳ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ በመግባት የዓለም ክብረወሰን ማሻሻሏ ይታወሳል።
ወደ በርሊን ከማምራቷ በፊትም በ2026 የለንደን ማራቶን የሴቶች ብቻ ክብረወሰንን በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በመግባት ለመስበር መብቃቷ የቅርብ ጊዜ ትልቅ ስኬቷ ነው።
በአዘጋጆቹ ግምት መሠረት ትዕግሥት በዘንድሮው ውድድርም 2 ሰዓት ከ09 ደቂቃ በታች የኾነ ፈጣን ሰዓት ልታስመዘግብ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።
ለዚህም እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት መካከል ከለንደን ድሏ በኋላ የተናገረችው አስተያየት ይገኝበታል። አትሌቷ «በቀደሙት ውድድሮች የፍጥነት ልምምዴን በከፊል ለመቀነስ እገደድ ነበር፤ ዘንድሮ ግን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ሆኜ ነው የመጣሁት። በፍጥነቴ ላይ በደንብ ለመሥራት በመቻሌ እና በፈጣን አጨራረስ ማሸነፌ እጅግ አስደስቶኛል» በማለት መናገሯ ይታወሳል።
ለአዘጋጆቹም «በድጋሚ የዓለም ክብረወሰኑን ለመስበር በጉጉት የበርሊን ጎዳናዎችን እጠብቃለሁ» ስትል ገልጻለች።
ትዕግሥት አሰፋ በ2023 በርሊን ላይ ያስመዘገበችውን የድብልቅ ማራቶን የዓለም ክብረወሰን በ2024 በኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች 2 ሰዓት ከ09 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ የተቀማች ሲኾን፣ ይህንን ሰዓት በመስበር ክብረወሰኑን እንደገና በእጇ ለማስገባት ትፎካከራለች። የምቹ አየር ሁኔታ፣ ወንድ አሯሯጮች መኖራቸው እና የራሷ ወቅታዊ ብቃት ሰዓቱ ሊመዘገብ እንደሚችል ተስፋ ሰጥቷል።
በውድድሩ የትዕግሥት ዋና ተፎካካሪ የምትኾነው ባለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ ኬንያዊት ሮዝመሪ ዋንጂሩ ናት። ከሁለቱ በተጨማሪ አማኔ በሪሶ፣ በዳቱ ሂርጳ፣ ደራ ዲዳ፣ ዘይነባ ይመር፣ ቦሰና ሙላቴ፣ ምስጋጋ አለማየሁ፣ በቀለች ጉደታ፣ ጋዲሴ ሙሉ፣ አሚነት አህመድ፣ ኢቢሴ አዱንያ እና አለምአዲስ እያሱ በውድድሩ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
በዘንድሮው የበርሊን ማራቶን ከ160 ሀገራት የተወጣጡ ከ60 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ።
ዘጋቢ፦ ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



