በወንዶች 5 ኪሎ ሜትር አዲሱ ይሁኔ እና መዝገቡ ስሜ ከዓለም አቀፍ ኮከቦች ጋር ይፋለማሉ።

0
114

 

በዴንማርክ ኮፐንሃገን ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና መክፈቻ ቀን ከሚከናወኑት ዋና ዋና የሩጫ ዓይነቶች መካከል የወንዶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድር አንዱ ሲኾን አትሌት አዲሱ ይሁኔ እና አትሌት መዝገቡ ስሜ ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ወክለው ይሰለፋሉ።

ከበሪሁ አረጋዊ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ በመቀጠል በርቀቱ ፈጣን ሰዓት ያለው ፈረንሳዊው አትሌት ጂሚ ግሬሰር የማሸነፍ ከፍተኛ ቅድመ ግምት አግኝቷል።

የኖርዌዩ የርቀት ውድድር ኮከብ ያኮብ ኢንግብሪስተን የውድድሩ ሌላኛው ዋና ተፎካካሪ ነው።

በብራሰልስ የ5000 ሜትር ፍጻሜ ኢንግብሪስተንን ተከትሎ የገባው የብሩንዲው አትሌት ለርቀቱ ፉክክር ተጨማሪ ድምቀት እንደሚኾን ተጠብቋል።

አዲሱ ይሁኔ ባለፈው ሚያዚያ ወር በፈረንሳይ ሊል በተካሄደው ውድድር 12 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ በመግባት ከጂሚ ግሬሰር በመቀጠል 2ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል። ይህም ሰዓት በዓለማችን 5ኛው ፈጣን ሰዓት ኾኖ ተመዝግቧል። በዲያመንድ ሊግ ፍጻሜ ለመሰለፍ የሚያስፈልገውን ነጥብ ቢያስመዘግብም በመለስተኛ ሕመም ምክንያት ሳይሰለፍ የቀረ ሲኾን በአልቲሜቱ ደግሞ በተፈጠረ መገፋፋት በመውደቁ ውድድሩን ሳያጠናቅቅ ቀርቷል።

አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በማገገም ለሀገሩ ክብር ከጠንካራ አትሌቶች ጋር ለመፋለም በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ይገኛል።

መዝገቡ ስሜ በዘንድሮው የዲያመንድ ሊግ እና በዙር ውድድሮች ውጤታማ አፈጻጸም ሲያሳይ የቆየ ሲኾን ባለፈው ሚያዚያ ወር በቦስተን 5 ኪሎ ሜትር ውድድር 13 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ በማስመዝገብ አዲሱ ይሁኔን ተከትሎ 2ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።

በውድድሩ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግ ሲኾን፣ በጣም ፈጣን ሰዓት እንደሚመዘገብም ይጠበቃል።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#አዲስ_አበባ #መስከረም_09_2019_ዓ_ም

በሐናማርያም መስፍን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here