ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የተገነባው እና ከ50 ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠው የባሕር ዳር አጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እድሳት እየተደረገለት ይገኛል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት ሥራ አሥኪያጅ ተሻገር አዳሙ የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ግንባታዎች ከሚያካትታቸው አንዱ የኾነው የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም በሁለት ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ተደርጎ እየተገነባ መኾኑን ገልጸዋል።
የስታዲየሙ ግንባታ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ እና የመሮጫ ትራክን ያካተተ ነው። ነባሩ ክቡር ትሪቡን ፈርሶ በአዲስ ይተካል ተብሏል።
የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት አማካሪ መሀንዲስ ኢንጅነር ሀብታሙ መላኩ ስታዲየሙ የመጸዳጃ፣ የሻወር እና የተጫዋቾች ልብስ መቀየሪያ ክፍልን ያሟላ መኾኑን ተናግረዋል።
የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም የእድሳት ግንባታ አብዛኛው ሥራው በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። ሰው ሠራሽ ሳር የሚነጠፍለት የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም እስከ 18 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ ነው። ስታዲየሙ ከጣና ሐይቅ ነፋስ እንዲያገኝ ሲባል በደሴት ሎጅ እና በግራንድ ሆቴል መካከል ክፍት ቦታ እንዲኖረው መደረጉንም አስታውቀዋል።
በርካታ ውድድሮችን ያስተናገደው ታሪካዊው የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም የእድሳት ሥራው ሲጠናቀቅ የፕሪምዬር ሊግ እና ሌሎች ውድድሮችን ከማስተናገድ ባለፈ ለባሕር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም አጋዥ ኾኖ ያገለግላል ተብሏል።
የስታዲየሙ እድሳት ሲጠናቀቅ ለባሕር ዳር ከተማ አንዱ የመስህብ አካል እንደሚኾን ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- መልሰው ጥበቡ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ



