በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ ከቅንጦትነት ወደ ዋና የውድድር መሣሪያነት የተሸጋገረው የቪዲዮ ትንተና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስፖርቱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ቢኾንም የኢትዮጵያ ክለቦች ግን አሁንም ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጡት ተገልጿል።
የካፍ ኢንስትራክተር አሠልጣኝ እና የቪዲዮ ትንተና ባለሙያው መብራቱ ሀብቱ እንደገለጹት የቴክኖሎጂው ዕድገት የጨዋታዎችን ዝርዝር እንቅስቃሴ በምስል እና በመረጃ (ዳታ) አስደግፎ ለመተንተን ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
ይህ አሠራር የተጋጣሚ ቡድንን የጨዋታ ስልት ለመተንተን እንዲሁም የራስን ቡድን እና የተጫዋቾችን ብቃት በትክክል ለመገምገም ያስችላል።
የቪዲዮ ትንተና ለተጫዋቾች ዕድገት የሚሰጠውን ጥቅም ሲያብራሩም፦
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ክለቦች እና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በውስን ደረጃም ቢኾን ባለሙያዎች የሚገኙ ቢኾንም አደረጃጀቱ አሁንም ሰፊ ክፍተቶች ያሉበት መኾኑን ጠቁመዋል።
በመኾኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች ለይስሙላ ሳይኾን ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር የቪዲዮ ትንተና ባለሙያዎችን በቋሚነት እንዲቀጥሩ ማስገደድ እንዳለበት አሠልጣኝ መብራቱ አሳስበዋል።
ይህ አሠራር ተግባራዊ ሲደረግ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾችን ማፍራት እና ለሀገር የሚጠቅም ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት እንደሚቻልም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ዳናይት ሲሳይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



