ኮሚዩኒቲ ሺልድ በእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር አዘጋጅነት በየዓመቱ የአዲሱን የውድድር ዘመን ማብሰሪያ ኾኖ የሚካሄድ ጨዋታ ነው።
ጨዋታው በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ እና የኤፍ ኤ ካፕ አሸናፊዎች የሚገናኙበት ነው።
አንድ ክለብ ሁለቱንም ዋንጫዎች በአንድ የውድድር ዘመን ካሸነፈ ግን በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቡድን በውድድሩ ላይ ይሳተፋል።
አብዛኛውን ጊዜ በታዋቂው የለንደኑ ዌምብሊ ስታዲየም የሚካሄደው ይህ ጨዋታ ቀደም ሲል “ቻሪቲ ሺልድ” በመባል ይታወቅ ነበር።
ከትኬት እና ዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ በእንግሊዝ ለሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ለማኅበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶች የበጎ አድራጎት ዓላማ ይውላል።
ነገ የእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ የ2025/26 አሸናፊው አርሰናል እና የኤፍኤ ካፕ አሸናፊው ማንችስተር ሲቲ በኮሚዩኒቲ ሺልድ ትልቁን ፍልሚያ ያደርጋሉ።
ማንችስተር ሲቲ ባለፈው ሚያዝያ ወር በፕሪምየር ሊጉ አርሰናልን 2ለ1 ካሸነፈ ወዲህ ሁለቱ ተቀናቃኞች የሚያደርጉት የመጀመሪያ ግንኙነት በመኾኑ ጨዋታው ትልቅ ትኩረትን ስቧል።
ቡድኖቹ በዋንጫ ውድድር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ2026 የካራባኦ ካፕ ፍጻሜ ነው። በወቅቱ ኒኮ ኦራይሊ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ማንችስተር ሲቲ አርሰናልን 2ለ 0 በመርታት አሸናፊ መኾኑ ይታወሳል።
ሁለቱ ቡድኖች በኮሚዩኒቲ ሺልድ ደግሞ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ2023 ነው። በመደበኛ ጨዋታ 1 አቻ ካጠናቀቁ በኋላ በመለያ ምት አርሰናል 4ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል።
በዚህ ውድድር ማሸነፍ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ሥነ ልቦናዊ የበላይነትን ቢያጎናጽፍም ታሪክ ግን ከዚህ የተለየ እውነታን ያሳያል።
ይልቁንም የኮሚዩኒቲ ሺልድ አሸናፊ መኾን አንዳንዴ በሊጉ ስኬታማ ላለመኾን እንደ እርግማን ሲቆጠር ይታያል።
በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ባለፉት 16 ዓመታት የኮሚዩኒቲ ሺልድ እና የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎች ማሸነፍ የቻለው እ.ኤ.አ በ2018/19 ማንችስተር ሲቲ ብቻ ነበር።
በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ከ1992 ወዲህ ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው በስምንት አጋጣሚዎች ብቻ ነው።
በአንድ የውድድር ዓመት ሁለቱንም ክብሮች 5 ጊዜ በማንሳት ማንችስተር ዩናይትድ ቀዳሚ ነው፣ ቼልሲ በ2005/06 እና 2009/10፣ ማንችስተር ሲቲ በ2018/19 ይህንን ድል የተቀዳጁ ክለቦች ናቸው።
ነገ የሚደረገው የኮሚዩኒቲ ሺልድ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በካርዲፍ የሚደረግ ይኾናል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ታዋቂው ድምጻዊ ዘ ዊክንድ የሙዚቃ ኮንሰርት በዌምብሊ ስታዲየም ስለሚያቀርብ ነው።
ይህም ጨዋታው እ.ኤ.አ ከ2007 ወዲህ ከዌምብሊ ስታዲየም ውጪ የሚካሄድበት ሦስተኛው አጋጣሚ ያደርገዋል።
በውድድሩ ታሪክ ማንችስተር ዩናይትድ 21 የኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚ ነው። አርሰናል 17፣ ሊቨርፑል 16 ጊዜ ባለድል መኾን ችለዋል።
#አሚኮ #ስፖርት
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_09_2018ዓ_ም
በሀብታሙ ዳኛቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



