ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ዛሬ ምሽት 4:00 ላይ በቦስተን ስታዲየም የሚደረገው የፈረንሳይ እና የኖርዌይ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
ሁለቱም ሀገራት ባደረጓቸው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ 6 ነጥብ በመሰብሰብ ወደ 32ቱ የጥሎ ማለፍ ዙር ማለፋቸውን ቀድመው ማረጋገጣቸው ይታወሳል። ኾኖም የዛሬው ጨዋታ ዋጋው ቀላል አይደለም፤ የምድቡን አንደኝነት ይዞ ለማጠናቀቅ የሚደረግ የክብር እና የብቃት መለኪያ ጨዋታ እንደሚኾን ይጠበቃል።
የዚህ ጨዋታ ዋነኛ መነጋገሪያ ነጥብ በቡድኖቹ ስብስብ ውስጥ የሚገኙት አጥቂዎች ጉዳይ ነው። ኪሊያን ምባፔ በውድድሩ ላይ አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት በሁለቱ ጨዋታዎች 4 ግቦችን በማስቆጠር የፈረንሳይን የፊት መስመር በበላይነት እየመራ ይገኛል።
ኧርሊንግ ሀላንድ ለሀገሩ ኖርዌይ በተመሳሳይ 4 ግቦችን ያስቆጠረ አስፈሪ አጥቂ ነው። በተለይ በሴኔጋል ላይ ያስቆጠራት ሁለተኛዋ ግብ ኖርዌይን ለዚህ ደረጃ አብቅቷታል። የሁለቱ አጥቂዎች ፍጥጫ እና በጨዋታው የበላይ ኾኖ ለመገኘት የሚደረገው ፉክክር ትኩረትን ስቧል።
በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ምሽት 4:00 ላይ ሴኔጋል ከኢራቅ የሚጫወቱ ይኾናል።
በሌላ ጨዋታ ለሊት 9:00 ላይ ኡራጓይ ከስፔን ይጫወታሉ። ስፔኖች ወደ ጥሎ ማለፉ ውስጥ ለመግባት ሰፊ ዕድል ቢኖራቸውም፣ የምድቡን አንደኝነት ይዞ ለማጠናቀቅ ዛሬም ቢኾን ጨዋታውን በቀላሉ እንደማይመለከቱት ይጠበቃል።
ባለፉት ጨዋታዎች 44 ሙከራዎችን አድርጋ ግብ ማስቆጠር ያቃታት ኡራጓይ ዛሬ በዳርዊን ኑኔዝ መሪነት የላቀ ብቃት ማሳየት ይኖርባታል።
በዚህ ምድብ በተመሳሳይ ለሊት 9:00 ላይ ኬፕ ቬርዴ ከሳውዲ አረቢያ ይጫወታሉ።
ሌሎች የምድብ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ በተመሳሳይ ጠዋት 12:00 ላይ ኒውዝላንድ ከቤልጅየም እና ግብፅ ከኢራን ይጫወታሉ።
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት
በሳሙኤል ጥሩነህ (የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአሚኮ የተግባር ተማሪ)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



