“የ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ እና ወንድማማች ተጨዋቾች”

0
51

 

አዲስ አበባ: ግንቦት 30/2018(አሚኮ) ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚጀመረው የዓለም ዋንጫ ላይ ከስምንት ቤተሰብ የተገኙ ወንድማማቾች ተሳታፊ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ከአራት ቤተሰብ የተገኙ ወንድማማቾች የተለያየ አገርን ይወክላሉ።

የ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ውድድር በውሥጡ ስምንት የተረጋገጡ የወንድማማች ጥንዶችን በማካተት ብርቅዬ የኾነ የቤተሰብ ትስስር ታሪክን ይዞ ይቀርባል። አንዳንዶቹ የአንድ ቡድን መልበሻ ክፍልን ይጋራሉ። ሌሎች ደግሞ የውድድሩ ዕጣ አደላደል በሚፈቅደው መሠረት፣ በዚኹ የዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ በተቃራኒ ጎራዎች ላይ ተሰልፈዋል።

በጣም ትኩረት የሚስቡት ጉዳዮች በመጀመሪያ የሚጠቀሱት ናቸው፤ ምክንያቱም አራት ቤተሰቦች ልጆቻቸው የተለያየ አገር ወክለው ሲጫወቱ የሚመለከቱ በመኾናቸው፣ ይህ የዘር ሐረግ እና የዓለም አቀፍ ቡድን ምርጫ ውሳኔ በውድድሩ ላይ ትልቅ ሰብዓዊ ትርጉም ካላቸው ኹነቶች አንዱ እንዲሆን ያደርገዋል።

ከዱዌ ወንድማማቾችን እንጀምር፣ የስትራስቡርጉ ቀኝ ተከላካይ ጌላ ዱዌ እና የፒ ኤስ ጂው ዲዚሬ ዱዌ ከአንድ እናት አባት ተወልደው ለተለያዩ ሀገራት ይጫወታሉ:: ጌላ ዱዌ ኮትዲቩዋርን ሲወክል፣ የፒ ኤስ ጂው የክንፍ መስመር ተጫዋች ዴዚሬ ዱዌ ደግሞ ለፈረንሳይ ይጫወታል። ጌላ ለአገሩ 21 ጨዋታዎችን አድርጎ 4 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ዴዚሬ ደግሞ ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን 6 ጨዋታዎችን አድርጎ 2 ጎሎችን አስቆጥሯል። በቅርብ በወዳጅነት ጨዋታ ኮቲዲቮር ፈረንሳይን 2-1 ስታሸንፍ ጌላ ዱዌ ጎል ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው::

ሌላው በተለያየ ሀገር አለም ዋንጫ ላይ የተወከለው ቤተሰብ የዊሊያምስ ወንድማማቾች ነው:: የዊሊያም ቤተሰብ አሁንም በትልቅ ስም የሚጠቀሱት የተለያዩ አገራትን የመረጡ ወንድማማቾች ናቸው። ኢናኪ እና ኒኮ ዊሊያምስ ሁለቱም ለአትሌቲክ ክለብ የሚጫወቱ ቢኾንም፣ ኢናኪ ጋናን መርጦ ከ25 በላይ ጨዋታዎችን በማድረግ 2 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ ኒኮ በበኩሉ ስፔንን በመወከል 30 ጨዋታዎችን አድርጎ 6 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲኾን፣ ከአገሩ ጋር የ2024 የዩሮ ዋንጫን ማንሳት ችሏል።

የጋናው መሃል ተከላካይ ዴሪክ ሉካሰን እና የኔዘርላንድሱ አጥቂ ብራያን ብሮቤይ ወንድማማቾች ናቸው፤ ሉካሰን በፓፎስ ክለብ ውስጥ የሚጫወት ሲኾን፣ ብሮቤይ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ሰንደርላንድ እየተጫወተ ለብሔራዊ ቡድኑ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ 1 ጎል አስቆጥሯል።እነዚህ ወንድማማቾችም በተለያዩ ብሄራዊ ቡድኖች ሀገርን ይወክላሉ::

የሱታር ወንድማማቾች በአለም ዋንጫው የተለያየ ሀገር በመወከል የተጠቀሰ ሌላው ቤተሰብ ነው ። ጆን ሱታር ለስኮትላንድ የሚጫወት ሲሆን፣ ሃሪ ሱታር ደግሞ አውስትራሊያን ይወክላል፤ በዋና ዋና ውድድሮች ላይ መደበኛ ተጫዋች በመሆኑም በአውስትራሊያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው።

እነዚህ ወንድማማቾች የተለያየ ሀገር ወክለው መጫወታቸውን አነሳን እንጅ ለአንድ አገር የሚጫወቱት ወንድማማቾችም በርካታ ናቸው።

ከእነዚህም መካከል ሉካስ ሄርናንዴዝ እና ቴዎ ሄርናንዴዝ ሁለቱም ፈረንሳይን ይወክላሉ፤ የፒኤስጂው ሉካስ የ2018 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሲሆን፣ የአል-ሂላሉ ቴዎ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በግራ ተከላካይነት ተመራጭነቱ ከፍ ያለ ተጫዋች ነው።

ኔዘርላንድስ በበኩሏ ኩዊንተን እና ዩሪየን ቲምበር አሏት፤ የማርሴዩ አማካኝ ኩዊንተን አሁንም ቦታውን ለማስከበር እየታገለ ሲሆን፣ የአርሰናሉ ተከላካይ ዩሪየን ግን የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ይበልጥ የታወቀ ስም አለው።

ኬፕ ቨርዴ የፑስካሽ አካዳሚውን ላሮስ ዱአርቴ እና የሉዶጎሬትሱን ዴሮይ ዱአርቴ የያዘች ሲሆን፣ሊአንድሮ እና ጁኒንሆ ባኩና በኩራሳኦ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወንድማማቾች ናቸው።

ያሆ ስፖርት በዘገባው እንዳመላከተው በዚህ አለም ዋንጫ የምንመለከታቸው ስምንት ወንድማማቾች የውድድሩ ትኩረት ይሆናሉ ብሏል።

በቴዎድሮስ ኅ/ኢየሱስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here