ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እስከ ዛሬ በተካሄዱት 22 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች የተሳተፈችው ብራዚል አምስት ጊዜ ዋንጫውን አንስታለች፡፡
20 ጊዜ የተሳተፈችው ጀርመን አራት ጊዜ ሻምፒዮን ኾናለች፡፡ 18 ጊዜ የተካፈለችው አርጀንቲና ሦሥት ጊዜ ለሻምፒዮናነት በቅታለች፡፡
ከእነዚህ እና መሠል ባለታሪክ ሀገራት በላይ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች በጨዋታ ሲሰላ ከፍተኛ ግብ በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ግን እዚህ ግባ የሚባል የውጤታማነት ታሪክ የሌላት ሀንጋሪ መኾኗ አስገራሚ ኾኗል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን ከ1986 በኋላ በተካሄዱት ዘጠኝ ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ማጣሪያውን እንኳን ማለፍ ተስኗት ያልተሳተፈችው ሀንጋሪ ካደረገቻቸው ጨዋታዎች አንጻር ባስቆጠረቻቸው ግቦች ስሌት በጨዋታ በአማካይ 2 ነጥብ 72 ግብ በማስመዝገብ ቀዳሚ ናት፡፡
ሀንጋሪን ለዚህ ክብር ያበቃት በሦሥት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ብቻ (1938፣1954 እና 1982) በጥቂት ጨዋታዎች ያዘነበችው ግብ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሀገሪቱ በ1938ቱ የዓለም ዋንጫ እስከ ፍጻሜ ተጉዛ በጣሊያን 4 ለ 2 ተሸንፋ ዋንጫውን አጥታለች፡፡ ነገር ግን እስከ ፍጻሜ ባለው ጉዞዋ 15 ግቦችን አስቆጥራለች፡፡
ከእነዚህም መካከል በመጀመሪያው ዙር ደች ኢስት ኢንዲስን 6 ለ 0፣ ግማሽ ፍጻሜ ላይ ስዊድንን 5 ለ 1 የረታችባቸው ይጠቀሳሉ፡፡
ከ16 ዓመታት በኋላ በተካሄደው የዓለም ዋንጫም ለሻምፒዮናነት ብትበቃም እስከ ፍጻሜ የዘለቀችው ሀንጋሪ በዚህ ጉዞዋ 27 ግቦችን በማስቆጠር በአንድ የዓለም ዋንጫ የከፍተኛ ግብ ባለቤትነት ክብረ ወሰንን ጨብጣለች፡፡
በተለይ በወቅቱ ደቡብ ኮሪያን 9ለ0 የረታችበት ውጤት በዓለም ዋንጫው ታሪክ በአንድ ጨዋታ የተመዘገበ የሰፊ ግብ አሸናፊነት ክብረ ወሰን ባለቤት አድርጓታል፡፡
በ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ደግሞ ኤል ሳልቫዶርን 10ለ1 የረታችበት ጨዋታ የራሷን እና የዓለም ዋንጫውን የሰፊ ግብ ድል ክብረ ወሰንን ያሻሻለ ኾኗል፡፡
እንደ ያሁ ስፖርትስ ዘገባ ከኾነ በአጠቃላይ በተሳተፈችባቸው ውስን የዓለም ዋንጫ መድረኮች 32 ጨዋታዎችን አድርጋ 87 ግቦችን ያስቆጠረችው ሀንጋሪ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2 ነጥብ 72 ግብ በማስቆጠር የበላይነቱን ይዛ ትገኛለች፡፡
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_እግር_ኳስ
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



