🏟️⚽️ ለታሪካዊው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፍልሚያ ‘በሦስቱ ሰማያት’ ሼር ያለ ዝግጁነት !

0
52

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ)⚽️ በእግር ኳሱ ዓለም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በይዘቱ እና በስፋቱ ግዙፍ የኾነ አዲስ ምዕራፍ ሊቀመጥ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተዋል።

የ2026 ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድርን አዘጋጆቹ ሦስቱ ጎረቤታማ ሀገራት (አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ) እጃቸውን ዘርግተው የጨዋታው ታዳሚ እንግዶችን እና የዓለምን የእግር ኳስ ክብር ለመቀበል ቀድመው ደጃፋቸውን ከፍተዋል።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (FIFA) ያመጣው አዲስ መዋቅር የ2026 የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድርን ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል።

ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበር የመረጃ ቋት እንዳገኘነው መረጃ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ የቡድኖቹ ቁጥር ከ32 ወደ 48 አድጓል። ይህም ተጨማሪ የዓለም ሀገራት የህልማቸው ተካፋይ እንዲኾኑ አስችሏል ይላል መረጃው።

የ39 ቀናት ቆይታ በሚኖረው ውድድር ውስጥ 104 ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ውድድሩ ረጅም፣ አድካሚ እና የጽናት መለኪያ ቢኾንም ለአሸናፊው የሚሰጠው ክብር ግን ወደር የሌለው እንደኾነ እየተገለጸ ይገኛል።

ሰኔ 11/2026 በሜክሲኮው ታሪካዊ ስታዲየም (Estadio Azteca) የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታ መክፈቻው ፊሽካ ሲነፋ መላው ዓለም በአንድ ትንፋሽ መመልከት ይጀምራል። በሦሥቱ ሀገራት ለዚህ ውድድር የተመረጡት 16 ከተሞች እና ስታዲየሞች እጅግ ዘመናዊ እና የቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ያረፈባቸው ናቸው።

በአሜሪካ የሚገኙ አብዛኞቹ ግዙፍ ስታዲየሞች የተገነቡት ለአሜሪካን እግር ኳስ ጨዋታ (NFL) በመኾኑ መሬታቸው በሰው ሠራሽ ሳር የተሸፈነ ነበር። ፊፋ ደግሞ ለዓለም ዋንጫ ፍጹም የተፈጥሮ ሳርን በዋና መስፈርትነት ያስቀምጣል። ይህም አጋጣሚ ፈታኝ ኾኖ ነበር። ባለፉ ወራት ግን በስታዲየሞቹ ውስጥ ተአምር ተሠርቷል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም ስታዲየሞች ውስጥ ልዩ እንክብካቤ የተደረገለት ለምለም የተፈጥሮ ሳር ተተክሎ አረንጓዴው ምንጣፍ ለእግር ኳሱ ግብግብ ዝግጁ ኾኗል። መቀመጫዎችም ተስፋፍተዋል።
ግዙፍ የኤችዲ ስክሪኖች ተገጥመዋል። ስታዲየሞቹ የነገሥታትን መምጣት የሚጠባበቁ ቤተ-መንግሥቶችን መስለዋል።

ፊፋ በቅርቡ ይፋ ያደረገው የ1 ሺህ 248 ተጫዋቾች ስብስብ የውድድሩን ናፍቆት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል። የዘመናችን የምንግዜም ምርጥ ተጫዋቾች ተብለው የሚታሰቡት ሊዮኔል ሜሲ እና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ አሁንም በሀገራቸው ስብስብ ውስጥ መካተታቸው ውድድሩን የታላላቆች የመጨረሻው የስንብት መድረክ ያደርገዋል።

ከአዳዲሶቹ ወጣት ኮከቦች ፍልሚያ ጎን ለጎን የእነዚህ አንጋፋዎች ክህሎት በሰሜን አሜሪካ ምድር ላይ ታሪክ ይጽፋል።

ከአትላንቲክ እስከ ፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻዎች፤ ከካናዳው ቅዝቃዜ እስከ ሜክሲኮው ሙቀት፤ ከኒው ዮርክ የምድር ውስጥ ባቡሮች እስከ ሜክሲኮ ሲቲ አደባባዮች፤ ከቶሮንቶ ጎዳናዎች እስከ ሎስ አንጀለስ የባሕር ዳርቻዎች ድረስ ደጋፊዎችን ለመቀበል የትራንስፖርት እና የጸጥታ መዋቅሩ ዝግጁነት ተጠናቋል።

ልዩ የደጋፊዎች መዝናኛ ቀጠናዎች ተዘጋጅተዋል። ዓለም አቀፉ የስፖርት ማኅበረሰብ በአሁኑ ወቅት ዓይኑን ወደ ሰሜን አሜሪካ አዙሯል፤ ዝግጅቱም አልቋል። መድረኩ ተመቻችቷል።

የጨዋታው ዋና ተዋናዮችም ሽንጣቸውን ገትረው ፍልሚያውን እየተጠባበቁ ይገኛል። አሁን የሚቀረው አንድ ነገር ብቻ ነው። የመክፈቻው ፊሽካ ብቻ!

በሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here