አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ግራን ፕሪ የአንድ ቀን ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።
ውድድሩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ኾኖ መግለጫ ሰጥቷል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር መክዩ መሐመድ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ይሄንን ውድድር ለማካሄድ አዘጋጁ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከመንግሥት ጋር በመኾን የአዲስ አበባ የመሮጫ መምን ዝግጁ በማድረግ በኩል አስደናቂ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ውድድሩ መዘጋጀቱ ዓለም አቀፋዊ ዘርፍ ኾኖ ብዙ ሴክተሮች ተሳታፊ የሚኾኑበት መኾኑ ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል። በስፖርቱ ሴክተር ያለውን ዘርፈ ብዙ ሀብት ከመጠቀም አኳያ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መሞከሩንም ጠቁመዋል።
ክፍተቶችን እያረሙ በቀጣይ ተመሳሳይ ውድድሮችን ወደ ሀገር ማምጣት ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ደረጃውን የጠበቀ መም በማዘጋጀት ውድድሮችን ለማምጣት መነሻ መሠረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ለዚህም ማሳያው ቅዳሜ የሚደረገው የአዲስ አበባ ግራን ፕሪ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ሌሎች ተመሳሳይ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ጥያቄዎችን ማቅረብ እና ማምጣት ቀጣይ የመንግሥት የቤት ሥራ ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስለሺ ስህን ኢትዮጵያ ውድድሩን በብቃት በማዘጋጀቷ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ ውድድሩን ለማከናወን ኮሚቴዎች ተቋቁመው በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ይህ መድረክ የነሐስ ደረጃ ውድድር ነው፤ በቀጣይ ደረጃውን ለማሳደግ በተለይም የወርቅ ደረጃ እንዲኾን ለማድረግ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
ተመልካች ወደ ስታዲየም መጥቶ እንዲመለከት እና ጥሩ ውድድር እንዲኾን እናድርግ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን ይሄንን ውድድር ለማዘጋጀት ስለበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የአትሌቶች መፍለቂያ በኾነችው ሀገር ይሄንን ውድድር ማድረግ ታሪካዊ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በቪዛ ምክንያት ውድድሮች ላይ ለመካፈል ለሚቸገሩ አትሌቶች ራሳቸውን ለማየት የሚጠቀሙበት ነው፤ ይሄም ትልቅ ዕድል ነው ሲሉ የነገውን መድረክ አስፈላጊነት ገልጸውታል።
በውድድሩ ከ13 ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ይካፈለሉ።
ዘጋቢ፦ ሐናማሪያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



