“3.86 በህይወቴ ትልቅ ትርጉም ፈጥሮ ህይወት ለማዳን አዘጋጅቶኛል” የሜዳሊያ ተሸላሚዋ ተመራቂ ዶክተር እጹብ ስንታየሁ

24

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት 92 የሕክምና ዶክተሮችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል 36ቱ ሴቶች ናቸው።

ዶክተር እጹብ ስንታየሁ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 3 ነጥብ 86 በማምጣት በሜዳሊያ ተመርቃለች።

3.86 ነጥብ በማምጣት የተመረቀችው ተማሪዋ “ውጤቱ በህይወቴ ትልቅ ትርጉም ፈጥሮ ህይወት ለማዳን አዘጋጅቶኛል” ነው ያለችው።

ያለፉት የትምህርት ዓመታት የኮቪድ ወረርሽኝ እና የተለያዩ ችግሮች የታለፉበት በዚያው ልክም ብዙ የተማርንበት እና ብዙ ያወቅንበት ነበር ብላለች።

ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የልፋቴን ዋጋ በማግኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ነው ያለችን።

የተማርንበት ሙያ ሰውን በማገልገል እና በማከም ላይ የተመሠረተ በመኾኑ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሕዝባችንን በማገልገል የሀገራችንን እና የሕዝባችንን አደራ ለመወጣት ቁርጠኞች ነን ብላለች።

በሕክምናው ዘርፍ በዚህ ወቅት መማር አዳዲስ በቴክኖሎጅ እና በዘርፉ አዳዲስ ዕውቀቶችን እንድናገኝ አስችሎናል ያለችን ተመራቂዋ ለኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፍ አዲስ ዕውቀት እና አቅም ይዘን ወደ ሥራው ዓለም በመሰማራት የተሻለ ነገር ለማበርከት ዝግጁ ነን ብላለች።

በምርቃት መርሐ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶክተር በቃሉ ውብሸት ዩኒቨርሲቲው በ12ኛ ዙር ያስመረቃቸው የሕክምና ዶክተሮች ለሀገሪቱ ሕክምና ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ናቸው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የዛሬውን ጨምሮ ያስመረቃቸው 1 ሺህ 457 የሕክምና ዶክተሮችን ሀገሪቱ ካሏት የሕክምና ዶክተሮች 10 በመቶ የሚኾነውን ይሸፍናሉ ነው ያሉት።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) የሕክምና ዲግሪያችሁ ማኅበረሰቡ በእጃችሁ ያስቀመጠው አደራ ነው ብለዋል።

በሰው ልጅ ህይወት ከውልደቱ እስከ ሞቱ ፊት ለፊት የምትገኙት እናንተ ሐኪሞች ናችሁ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በሕመሙና በፈውሱ እንድትደርሱለት አደራ ተሰጥቷችኋል ነው ያሉት።

ተመራቂዎቹ ሕክምናን የተማሩት ሕክምና ራሱ እየተፈተነ ባለበት ወቅት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ረጅሙን ጉዞ በትጋት እና በውጤት አጠናቃችኋልና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ዕለቱ ለተመራቂዎች ዕውቀትን ከመቀበል ዕውቀትን ወደ መፍጠር ደረጃ የተሸጋገሩበት ነው ብለዋል።

ተመራቂዎች ወደ ሥራው ዓለም የሚገቡት ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና መሰል ቴክኖሎጅዎች የትናንቱን የሕክምና መልክ በአዲስ መልክ እያደራጁ እና የአየር ንብረት ለውጥ የበሽታዎችን ሁኔታ እየቀየረ ባለበት ሁኔታ ነው ብለዋል።

ስለኾነም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን በጥበብ እና በዕውቀት በመጠቀም ለሕዝባቸው የላቀ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም የኢትዮጵያን የሕክምና ዘርፍ ወደፊት እንዲያራምዱ አደራ ብለዋል።

#ባሕርዳርዩኒቨርሲቲ#የሕክምናምረቃ
#ዶክተርእፁብስንታየሁ #ሜዳሊያተሸላሚ

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_19_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየባሕር በር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመርከቧ መልህቅ ነው።
Next articleየሳይበር ደኅንነት ለሀገር ሉዓለዊነት