
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ሦሥተኛዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት መኾኗን አመላክተዋል።
በቅርቡ በተደረገው የኢኮኖሚ ስሌት ማሻሻያ እና በምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት መሠረት የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) 210 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
ይህ አሐዝ ሀገሪቱ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ከደቡብ አፍሪካ እና ከናይጄሪያ ቀጥሎ በሦሥተኛ ደረጃ እንድትቀመጥ አስችሏታል።
👉በሁለት ከባድ ፈተናዎች መካከል የተመዘገበ ጉዞ፦
ይህ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ትኩረት የሚስበው ሀገሪቱ ታላላቅ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች ባለችበት ወቅት መመዝገቡ ነው።
የመጀመሪያው የባሕር በር እጦት እና የሎጂስቲክስ ጫና ነው።
በዓለም አቀፍ ንግድ እና ትራንስፖርት ላይ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትለው የባሕር በር እጦት የገቢ እና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴን ሲፈትን ቆይቷል።
ይህ ወጪ በመጨረሻ በገበያ ዋጋ እና በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ጫና አሳድሯል።
ሌላኛው የሰላም እና የፀጥታ መደፍረስ ሲኾን በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኀይሎች የሚፈጥሩት የፀጥታ ስጋት ለልማት ሥራዎች እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ሀገሪቱ የባሕር በር ባለቤት ስትኾን እና ሀብቷን በትክክል መጠቀም ስትችል የኢኮኖሚ ዕድገቷ ፍጥነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ይሸጋገራል።
ከባሕር ንግድ ጋር ያላት ትስስር ይጠናከራል፤ የወጪ እና ገቢ ንግድ ይሰፋል።
የሎጂስቲክስ እና የንግድ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ ሲያገኝ እና ያላትን ጸጋ በትክክል መጠቀም ስትችል በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ ቀዳሚዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት ትኾናለች ተብሎ ይጠበቃል።
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_19_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
