የሙስናን ስውር ትስስር በቴክኖሎጂ አሠራር ለመበጠስ እየተከናወነ ያለው ተግባር።

16

የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን 23ኛውን የፀረ ሙስና ቀንን በማስመልከት ከሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የምክክር መድረክ አካሂዷል።

“ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ” የሚለውም መሪ መልዕክቱ ነው።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ሙስና እና ብልሹ አሠራሮች የልማት ዕቅዶችን በማደናቀፍ የሕዝብ እምነትን ስለሚሸረሽሩ፣ ፍትሕን እና እኩልነትን ስለሚፈታተኑ ችግሩን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በባሕል ለውጥ መታገል ይገባል ብለዋል።

ሀብትን ከታለመለት ዓላማ ውጪ ማዋል የኑሮ ውድነትን እና የአገልግሎት ጥራትን ያጎድላል፤ በመኾኑም ብልሹ አሠራርን ለመከላከል እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማስፋት እና የሰው ኀይል ጣልቃ ገብነትን መቀነስ ወሳኝ እንደኾነ አስገንዝበዋል።

ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የፋይዳ ምዝገባን በከተማ እና በገጠር ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ማድረግ እና ሕዝቡን ማስገንዘብ ከሚዲያው እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

አቶ ዓባይ ችግሩን በሕግ ብቻ ሳይኾን በትምህርት እና በባሕል ለውጥ መቅረፍ ያስፈልጋል ብለዋል። የሕዝብ ግንኙነት እና የሚዲያ ባለሙያዎች እና መሪዎች ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ በበኩላቸው ሙስና በተደራጀ እና በተናበበ አቅም የሚፈጸም ወንጀል በመኾኑ የዘንድሮው መሪ ቃል ስውር ትስስሮችን በመበጠስ የሙስና ሰንሰለትን ማቋረጥ ላይ አተኩሯል ብለዋል።

ሙስናን ለመከላከል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስጀመር፣ የፋይዳ መታወቂያን ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር ማስተሳሰር፣ የኦንላይን ግዥ ሕግ መተግበር እና ያልተገባ ንብረት ማስመለስ አዋጅን ማጽደቅ የመሳሰሉ ሥርዓታዊ እርምጃዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

ሕዝብ ግንኙነት እና ሚዲያ ሕዝቡ ያለመጉላላት አገልግሎት እንዲያገኝ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የትውልድ ግንባታን በማገዝ እና ከባዶ ውግዘት ወጥተው በማስረጃ የተደገፈ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ መሥራት አለባቸውም ብለዋል።

አሚኮ ወቅታዊ አጀንዳዎችን በመፍጠር፣ ግንዛቤ በማስጨበጥ እና የአገልግሎት አሰጣጥን በመፈተሽ እየሠራ ላለው ተግባርም ምሥጋና አቅርበዋል።

✍️ በስማቸው አጥናፍ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_19_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የትግራይ ክልል ባለአደራ አሥተዳደርን የሥራ አፈጻጸም ገመገሙ።
Next articleየባሕር በር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመርከቧ መልህቅ ነው።