እርሷ አትደፈርም፤ ከሱ-35 ተዋጊ አውሮፕላኖች እስከ ዘመናዊ ድሮኖች ታጥቃለችና።

27

እርሷ የሉዓላዊነቷን ክብር ለማስጠበቅ እጅግ የላቁ እና የመጠቁ ቴክኖሎጂዎችን ታጥቃለች፤
የጠላትን ዓላማ ቀድማ ታውቃለች፣ ትለያለች፣ ትተነብያለች፣ ትተነትናለች፤ እንደ አስፈላጊነቱም ተመጣጣኝ ምላሽ ትሰጣለች።

ግዳጅን በቅጽበት መፈጸም የሚችሉ ግዙፍ የባሕር፣ የምድር፣ እና የአየር ወለድ ኀይሎች ባለቤት ናት። በየጊዜው አዲስ ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ ትጽፋለች፤ የጠላትን የጥፋት ሕልምም ገና ከሩቁ ታመክናለች።

ለቀጣናው አስተማማኝ የሰላም ዋስትና፣ የሉዓላዊነት ጋሻ እና የልማት ቀንዲል ናት፤ በፈጠራ እና በምርምር በመታገዝም ከፍ ያለ ወታደራዊ አቅም ገንብታለች።

እርሷን አትዳፈሯት፤ ለዜጎቿ መከበር አታንቀላፋምና። እሷን አትነሱባት፤ ለጠላት መድኃኒት ናትና። እርሷን አትነካኳት፤ የብሷም ኾነ የአየር ክልሏ እንዳይደፈር የሚያስችል ወታደራዊ ኀይል ገንብታለችና።

እርሷን አትፈታተኗት፤ ከረጅም ርቀት ተወንጫፊ መድፎች እስከ ዘመናዊ ታንኮች፣ ከሱ-35 ተዋጊ ጀቶች እስከ ድሮኖች፣ ከአየር መቃወሚያ ሥርዓቶች እስከ የሠለጠነ የሰው ኀይል ታጥቃለችና።

ከአየር ወደ አየር እና ከአየር ወደ ምድር ውጊያ የማካሄድ ከፍተኛ አቅምም ገንብታለች። እርሷን አታሲሩባት፤ የጠላትን እንቅስቃሴ በደቂቃዎች የሚያመክን አስፈሪ ኀይል ገንብታለችና፤ ይልቅስ አክብሯት፤ ለወደዳት በመከራ ጊዜ ደራሽ ናት፤ ለራበው አጉራሽ ናት፤ ለቀረባት መከታ ናት፤ ለቀጣናው ሰላም እና ደኅንነትም ዋስትና ናት።

ከውስጥ እና ከውጭ የተሸረቡ ሴራዎችን በበሰለ ስትራቴጂ የመፍታት ጥበብን ተክናለች።

እርሷ የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ አያስፈራትም፤ የዲፕሎማሲ ጫና አይበግራትም፤ ቀጣናዊ የጂኦፖለቲካ ውጣ ውረዶችም አያንበረክኳትም። ይልቁንም ያጀግናታል፤ ያበረታታል፤ ስኬትን ያጎናጽፋታል እንጂ፤ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተጋች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በምድር፣ በአየር እና በሳይበር ምኅዳሮች የላቀ እና አስተማማኝ የውጊያ አቅም ገንብታለች። ይህም የራሷን ሉዓላዊነት እና የሕዝቦቿን ሰላም እና ደኅንነት ከማስከበር ባለፈ የአፍሪካን ቀንድ ሰላም ለማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ አቅም ነው።

እርሷ በዓለም አቀፍ እና በቀጣናዊ የጂኦፖለቲካ ማዕበል ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ቀጥላለች፤ ብሔራዊ ጥቅሟን እና የቀጣናውን ጂኦፖለቲካዊ የበላይነት በጽናት እና በድል እያስከበረች ትገኛለች።

የአየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ “የኢትዮጵያ አየር ኀይል የሀገራችንን ሰማይ ሙሉ በሙሉ የመጠበቅ እና የመቆጣጠር ሙሉ ብቃት አለው፤ ‘ምድሩም፣ ሰማዩም፣ የብሱም የእኛ ነው!’ ስንል በተግባር በተረጋገጠ አቅም እና በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ዝግጁነት ላይ ተመሥርተን ነው” ብለዋል።

እናት ሀገራችን ብርድ እና ሐሩር የማይበግረው፣ ዳገት እና ቁልቁለት የማይገድበው የሠለጠነ የሰው ኀይል ገንብታለች። ነጻነቷን በክንዷ ያጸናች፣ ለባዕድ እና ለባንዳ እጅ የማትሰጥ የጀግኖች እልፍኝ ናት።

የባንዳን እና የባዕዳንን ተልዕኮ ጠንቅቃ ታውቃለች፤ የጠላትን የጦርነት ዝግጅት እና የጥፋት አጀንዳም ትተነብያለች።

እርሷ በአስተሳሰቡ የመጠቀ፣ በቴክኖሎጂ የላቀ፣ በሀገር ፍቅር ስሜት የተማረከ፣ በውጊያ ስልቱ የረቀቀ እና በወታደራዊ ሥነ ምግባር የታነጸ ሠራዊት ባለቤት ናት።

በእጅ አዙር ጦርነት ለመውጋት፣ ሰላሟን ለማናጋት እና የልማት ጉዞዋን ለማደናቀፍ የሚጥሩ የጥፋት ኀይሎችን የማምከን ጥበብን ተክናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ቢበዙባትም ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን ለማቀላጠፍ እና የቀጣናው ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን በብቃት ለማረጋገጥ እየሠራች መኾኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የውጭ እና የውስጥ ጠላት ኀይሎች የሚፈጥሩትን ማንኛውንም አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ እና የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ለመጠበቅ የሚያስችል ጽኑ መሠረትም እየጣለች ነው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ያላትን ድርሻ እና ባለቤትነት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያላትን የኀይል ሚዛን ለመቆጣጠር እየተጋች ትገኛለች ነው ያሉት።

✍️ ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_18_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article⚖️ የዕውነት እና የፍትሕ ሀገር በኾነችው ኢትዮጵያ የከሸፈው የግብጽ የተንኮል አዙሪት!
Next articleየማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ፦