
የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት እና የተፈጥሮ ጸጋዎቿን የመጠቀም መብት በቀጣናው ላይ የፖለቲካ ትኩሳት መፍጠሩ የግብጽን የበላይነት ሥነ-ልቦና በመበጣጠሱ የተፈጠረ እና ከታሪክ ማሕጸን የተቀዳ የሕልውና ስጋቷ መገለጫ ነው።
የግብጽ ጽንሰ-ሀሳባዊ መሠረት በኾነው “ግብጽ የዓባይ ስጦታ ናት” የተዛባ ትርክት ላይ የተመሠረተው የአሻጥር ስትራቴጂ፣ በውኃ ፖለቲካ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ጥናት እንደተገለጸው ኢትዮጵያን ማዳከም፣ የውስጥ ጸጥታዋን ማናጋት እና አግላይ የቅኝ ግዛት ውሎችን ማስቀጠል ብቸኛ የውኃ ደኅንነት ማረጋገጫ መንገዷ አድርጋዋለች።
የአስዋን ግድብን ስትገነባ ኢትዮጵያን ባለማማከር ያሳየችው ንቀት እና በቀጥታ ጦርነት ያጋጠማትን መሪር ሽንፈት የዘነጋችው ግብጽ፣ የታሪክ ፍርድ ተገልብጦ ዛሬ በኢትዮጵያ የልማት ድል ፊት ከከሸፈ ሰነባብቷል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግብጽን የዛቻ ድስኩር እና የኀይል ስጋት ሰብሮ በማጠናቀቅ ለቀጣናው የኀይል፣ የቱሪዝም እና የዓሣ ሀብት ማዕከል በመኾን ድልን ተቀዳጅቷል።
የኢትዮጵያ የድል አድራጊነት መንፈስ ወደ ቀይ ባሕር ፊቱን ሲያዞር ደግሞ የግብጽን የረዥም ጊዜ የጂኦ-ፖለቲካዊ ስጋት እውን አድርጎባታል። የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት የቀጣናውን የበላይነት ዳግም እንድትጎናጸፍ እና ዓለም አቀፋዊ የኀይል ሚዛን እንድትይዝ ያደርጋታል በሚል ስጋት ግብጽ አጋሮቿን በማስተባበር እና ታጣቂዎችን በመደገፍ የኢትዮጵያን የሕልውና ጥያቄ ለማክሸፍ ዛሬም ሌት ተቀን እየሠራች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ቀይ ባሕር እና ዓባይ የኢትዮጵያ የሕልውና መሠረቶች መኾናቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትፈልገውም ጦርነት ፈልጋ ሳይኾን በመርህ እና በሕግ ላይ በተመሠረተ የሰላም መንገድ የሕዝቧን ሕይወት ለመቀየር እንደኾነ አስረግጠዋል።
ኢትዮጵያ ያነገበቻቸው ግዙፍ የልማት አጋዥ ፕሮጀክቶች ርዕይ ግብጽ ለዘመናት የገነባችውን የማግለል እና የማዳከም ፖለቲካ ከሥሩ የሚያናጋም ነው።
በአጠቃላይ ግብጽ የቱንም ያህል የጥፋት ሤራ ብትጎነጉንም የዕውነት እና የፍትሕ ሀገር የኾነችው ኢትዮጵያ ከውስጥ ፈተናዎቿ ተሻግራ፣ አሻጥሮችን እያከሸፈች የጀመረችውን የብልጽግና እና የሉዓላዊነት ጉዞዋን ለማሳካት በትክክለኛው መንገድ ላይ ትገኛለች።
✍️ በስማቸው አጥናፍ
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_18_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
