4

የሀገር የመከላከያ ሠራዊት በየጊዜው ራሱን በቴክኖሎጂ በማዘመን፣ የላቀ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ግዙፍ ኾኖ ተገንብቷል። የመከላከል እና የማጥቃት አቅሙንም አይደፈሬ አድርጓል።

በወታደራዊ ሳይንስ እና በጥበብ ጎልብቷል። ሀገርን ከማይናወጥ የሰላም ማማ ላይ ለማስቀመጥ በቁርጠኝነት ይተጋል።

በእሳት የተፈተነ፣ የዘመነ ቴክኖሎጂን የታጠቀ፣ ከምድር እስከ አየር፣ ከባሕር እስከ ሳይበር ለኢትዮጵያ ክብር በጽናት የቆመ ነው። የጦር ቴክኖሎጂን በራስ አቅም ማምረት እና ማሻሻል ላይ በትኩረት ሠርቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር መከላከያ ሠራዊት እንደ ቤት ነው፣ በአንድ ምሶሶ ግንባታ አይቆምም እኩል መገንባት ይኖርበታል ብለዋል።

በቀላሉ ሸብረክ የማይል ተቋም እየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል። በዋና ጉዳዮች ተቋሙ ራሱን እንዲችል እየተሠራ ነውም ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቋም የራሱ ምግብ፣ ልብስ፣ ተተኳሽ በበቂ የሚያመርት ኾኗል ነው ያሉት። የዘመኑን የጦር ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅ መደረጉንም ገልጸዋል። የሠለጠነ ብቁ የሰው ኀይል መገንባትም ተችሏል።

የመከላከያ ሠራዊት ተቋም ባለፈው ዓመት በ100 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት ወደ ውጭ መላኩንም ገልጸዋል። ጥይት፣ ድሮን እና የአውሮፕላን ጥገናዎች ገቢ ማስገኘት ችለዋል ነው ያሉት። ተቋሙ የሚገነባው ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፣ ለቀጣናው ሰላም ነው ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለቀጣናው ታላቅ ወንድም እንደኾነም አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በቅርቡ የታጠቀቻቸው የጦር ጄቶችም ለጎረቤት ስጋት ሳይኾን ኩራት እንደሚኾንም ነው የጠቆሙት። እኛ የታጠቅነው ኢትዮጵያን እና ቀጣናውን ለመከላከል ነው ብለዋል።

በርቀት ማጥቃት ለመንግሥታት ብቻ ሳይኾን ለአሸባሪዎችም ቀላል ተግባር እየኾነ ስለመጣ ራሳችንን ለመጠበቅ እና ለጎረቤት ሀገራት ድጋፍ ለመስጠት ነው መከላከያው እየጎለበተ ያለው ብለዋል።

✍️ ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_18_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት፦