ከቤት ኪራይ ወደ ራስ ጎጆ _ የ1ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ብስራት

16

በየጊዜው ጣራ የሚነካው የቤት ኪራይ ዋጋ ከወቅታዊው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ የብዙ ቤተሰቦችን ኑሮ ሲያመሳቅል ቆይቷል። ዜጎች የራሳቸውን ጎጆ ለመቀለስ የሚያልሙት ሕልም በኪራይ ዋጋ ንረት የሚደናቀፍበት፣ በየጊዜው በሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ከሰፈር ሰፈር የሚንከራተቱበት እውነታ የብዙዎች የዕለት ተዕለት ፈተና ነው።

“የራስ ጎጆ” መኖሪያ ቤት ከግድግዳ እና ጣሪያ በላይ ነው፤ የመኖር ጥያቄ የቅንጦት ፍላጎት አይደለም። ይልቁንም የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር መገለጫ፣ የቤተሰብ ሰላም መሠረት እና የነገ ትውልድ ማሳደጊያ ዋስትና እንጂ።

ለዓመታት በከተሞች ፈጣን መስፋፋት እና በሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምክንያት ተንከባሎ የመጣው የመኖሪያ ቤት እጥረት እና የዜጎች ፍላጎት አንገብጋቢ ጥያቄን ወልዷል።

ታዲያ በኢትዮጵያ ከተሞች ለዓመታት የቆየውን የዜጎች ሥር የሰደደ የመኖሪያ ቤት ችግር በጊዜያዊ ማስታገሻ ሳይኾን በመሠረታዊነት ለመፍታት የመደመር መንግሥት ታሪካዊ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

የዚህ ታሪካዊ ጉዞ መነሻ የኾኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በኢነርጂ፣ በአቪዬሽን፣ በማዕድን እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የጀመረችውን የመቻል ጉዞ ወደ ዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ በማውረድ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን በመገንባት ለዜጎች ለማስረከብ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

ይህ ውጥንም የመንግሥትን ሕዝባዊ ወገንተኝነት እና የዜጎችን የኑሮ ጫና የማቅለል ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ ታላቅ ብስራት ነው።

ይህ ግዙፍ ሀገራዊ ንቅናቄ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የሚያነቃቃ እና ለብዙዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ብቻ ሳይኾን የመደመር መንግሥት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ክብር ለመጠበቅ እና ምቹ ሕይወት ለመፍጠር ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ምዕራፍ ነው።

የተወጠነው የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በቃል ላይ የቀረ ሕልም ሳይኾን ዛሬ ላይ በተጨባጭ ሥራ የታጀበ ሀገራዊ ንቅናቄ ኾኗል።

በመዲናችን አዲስ አበባ የተጀመሩት ከ100 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ መድረሳቸው ፕሮጀክቱ በምን ያህል ፍጥነት እና ቁርጠኝነት እየተመራ እንደኾነ ሕያው ምስክር ነው።

ይህ የዜጎችን ክብር ማዕከል ያደረገ ሰው ተኮር የመሠረተ ልማት ዕይታ በቀጣይ በክልል ከተሞች እና በገጠር አካባቢዎች ለሚሰፋው ሥራ ፈር ቀዳጅ ኾኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ውስጥ እየተገነቡ ያሉ ከ100 ሺህ በላይ ቤቶችን በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት ዜጎች ቤት ገንብተው የሚኖሩበት ዕድል ተመቻችቷል።

ይህንኑ እውን ለማድረግም በብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ተፈርሟል።

ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ከኪራይ ገንዘብ ባልበለጠ ክፍያ የራሳቸው ቤት ባለቤት እንዲኾኑ የሚያስችል የሞርጌጅ ሥርዓትም ተዘርግቷል።

የቤቶችን የመሸጫ ዋጋ ለዜጎች ተመጣጣኝ ለማድረግ እንደ ብረት፣ መስታወት እና ሴራሚክ ያሉ መሠረታዊ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ ተደርጓል።

ከዚህም ባለፈ የግል አልሚዎች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) ያሉ ዓለም አቀፍ አጋሮች በቅንጅት ወደ ሥራ ገብተዋል።

በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ እና በሕዝብ የተቀናጀ ጉልበት የተጀመረው የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ በቅርቡ የኪራይ ቤት ስጋትን ታሪክ አድርጎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን “እንኳን ለራሳችሁ ጎጆ አበቃችሁ” የሚያስብልበት ቀን ሩቅ አይኾንም።

✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_18_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየአፍሪካ ኩራት እና ምልክት
Next articleየቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት፦