
በረጅም ዘመናት ልህቀት እና በአፍሪካ ፈር ቀዳጅነት የታነጸው የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ ከአህጉራዊ ትስስር አንቀሳቃሽነት ባለፈ ለሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ቁመና ጠንካራ መሠረት ኾኖ እያገለገለ ይገኛል።
ይህንኑ ታሪካዊ አቅም ወደ ተጨባጭ ውሳኔ ሰጪነት በመቀየር ኢትዮጵያ በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው 43ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ጠቅላላ ጉባዔ ልዩ ስብሰባ ላይ 133 ድምፅ በማግኘት የድርጅቱ ምክር ቤት አባል ኾናለች። የምክር ቤቱ መቀመጫዎች ከ36 ወደ 40 ከፍ ሲሉ ከተጨመሩት አራት አዳዲስ ወንበሮች አንዱን ማግኘቷ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ፖሊሲ እና ደንብ አወጣጥ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራት ያስችላታል።
ይህ አባልነት የአፍሪካን የጋራ ጥቅም እና አንድነት ለማስከበር፣ የደቡብ-ለደቡብ ትብብርን በተግባር ለማጠናከር፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ተሰሚነት በዘላቂነት ለማሳደግ የምታደርገው ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ጥረት ተጨባጭ ውጤት ማሳያ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያን የመላው አህጉሪቱ ብቸኛ ዕጩ አድርጎ በመሰየሙ እና በአፍሪካ የሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) በመደገፉ የተገኘው ይህ አህጉራዊ ቅቡልነት በብሪክስ የትብብር ማህቀፍ ተጨማሪ ዓለምአቀፍ ድጋፍ አግኝቷል። ኢትዮጵያ ይህንን ውክልና እንደ ሀገር ስኬት ብቻ ሳይኾን የመላው አፍሪካን ጥቅም የማስከበር አህጉራዊ ኃላፊነት አድርጋ ወስዳዋለች።
በኒው ዴልሂ የተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ባወጣው የጋራ መግለጫ አንቀጽ 105 ላይ የአፍሪካ ኅብረትን ውሳኔ በመቀበል ለኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፉን ማረጋገጡም የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አድማስ ከአፍሪካ ባሻገር ያሰፋ ክስተት ነው። ይህም የአፍሪካ ኅብረት አህጉራዊ ውክልናን ሲሰጥ ብሪክስ ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ ኢኮኖሚዎች ዘንድ ሰፊ ፖለቲካዊ ዕውቅናን በማስገኘት ቀጣናዊ አንድነት እና የደቡብ-ለደቡብ ትብብር በዓለም አቀፍ የትብብር ማህቀፎች ውስጥ እንዴት ተደጋግፈው ውጤት እንደሚያመጡ በግልጽ ያሳያል።
ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ አህጉር ያለው ስትራቴጂካዊ ፋይዳ
በዚህ ወሳኝ የለውጥ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት ውስጥ ያገኘችው መቀመጫ ለሀገሪቱ፣ ለዜጎቿ እና ለመላው አፍሪካ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የአሠራር ፋይዳ አለው። በምክር ቤቱ ውስጥ ውክልና ማግኘቷ የበረራ ደኅንነት እና ጸጥታን፣ የአየር ትራፊክ አሥተዳደርን፣ የአካባቢ ጥበቃን እና የቴክኖሎጂ ፈጠራን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እና መመሪያዎችን (SARPs) በማርቀቅ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራት ያስችላታል።
በተጨማሪም ይህ አባልነት ኢትዮጵያ ከካርቦን ልቀት ቅነሳ፣ ከካርቦን ማካካሻ እና ከዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጆች ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎችን በመቅረፅ ረገድ ወሳኝ ድርሻ እንድትወጣ ያግዛታል። ይህም አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደንቦች ፍትሐዊ እንዲኾኑ፣ በአፍሪካ አየር መንገዶች እና በአዳጊ የአቪዬሽን ገበያዎች ላይ ያልተመጣጠነ የወጪ ጫና እንዳይፈጥሩ ለመከላከል ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።
የምክር ቤቱ አባልነት ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዲፕሎማሲን ከሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ጋር በቀጥታ የሚያስተሳስር ስትራቴጂካዊ ዕድል ነው። በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እየተስፋፉ ባሉ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቶች፣ በአየር ትራፊክ አገልግሎቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደራጁ የሥልጠና አካዳሚዎች የተደገፈው የአቪዬሽን ዘርፍ ሀገሪቱን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ዋነኛ ምሰሶ ኾኖ ያገለግላል።
በዓለም አቀፍ ደንብ እና አሠራር በቀጥታ መሳተፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የቁጥጥር ሥርዓት ላይ ያለውን እምነት በማጠናከር የአውሮፕላን ግዥ ፋይናንስ እና የኢንሹራንስ ወጪዎችን ይቀንሳል። ይህም አዲስ አበባ የአፍሪካ ተቀዳሚ የመንገደኞችና የጭነት መናኸሪያ እንድትኾን በማገዝ የወጪ ንግድን፣ የቱሪዝም እና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን፣ ለባለሙያዎች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን ያሳድጋል።
በአህጉር ደረጃ የኢትዮጵያ ውክል እና የአፍሪካን የጋራ የአቪዬሽን ፍላጎት ይበልጥ አካታች በኾነ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ ለማራመድ ጠንካራ መድረክ ከመፍጠሩም ባሻገር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከአፍሪካ የሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) ጋር በቅርበት በመሥራት የአፍሪካ የተቀናጀ የአየር ትራንስፖርት ገበያን (SAATM) የሚያፋጥኑ የአየር ክልል አሥተዳደርን የሚያቀናጁ፣ የአህጉሪቱን የእርስ በርስ ትስስር የሚያሰፉ እና የአባል ሀገራትን የቴክኒክና የደኅንነት አቅም የሚያጎለብቱ ፖሊሲዎችን በግንባር ቀደምትነት እንድታራምድ ያስችላታል።
ይህ ዓለም አቀፍ ውክልና የከፈታቸውን ዕድሎች ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር የአቪዬሽን ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍና ወጣት ባለሙያዎች ዝግጁነት ወሳኝ ድርሻ አለው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የተገኘውን የዲፕሎማሲ አቅም ወደ ዘላቂ ተቋማዊ ብቃት በማሸጋገር የኢትዮጵያን ብልጽግና እና የአፍሪካን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስር በዘላቂነት ያጠናክራል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_18_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
