
7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ግጭቶችን በሰላማዊ እና በንግግር መንገድ መፍታት የሥልጣኔ መገለጫ መኾኑን ተናግረዋል። ንግግር፣ ታጋሽነት እና ይቅር ባይነትን መላበስ ለሀገር ግንባታ እንደሚያግዝም ገልጸዋል። መንግሥት ከለውጡ ማግሥት አሸባሪ የተባለን ኀይል ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነትጥቁ ያስገባ መኾኑንም ተናግረዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት አሸንፈን ሰላምን በመምረጥ ለሰላም ተፈራርመናልም ነው ያሉት። የወጉንን ፈተናል፣ የወጉንን አቅፈን ለሀገር ሠርተናል ብለዋል። በርካታ ታጣቂዎች በየክልሉ የሰላምን አማራጭ እየተቀበሉ መኾኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ችግር እየተፈጠረ ያለው ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ እንድትኖር በሚፈልጉት ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ የመፈጸም አቅምም እንዳስፈራቸው ገልጸዋል።
የውስጥ ባንዳዎች ያልታጠቁ ዜጎችን በማጥቃት ታጋይ ለመኾን ይፈልጋሉ ብለዋል። ወታደር ሲያይ አራሽ ወታደር ሲዞር ክላሽ አንጋች ታጋይ ነው የተፈጠረ ብለዋል። ፊት ለፊት መዋጋት አይችሉምም ነው ያሉት። እርስ በእርስ እየተዋጋ ራሱን ይበላል ሲሉም የታጠቁ ኀይሎች ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
ብሔር ተበደለ ብላቹህ በየቦታው ያላችሁ ታጣቂዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ቋንቋየ፣ ባሕሌ ይከበር፣ ራሴን ላስተዳድር አለ እንጅ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር አልኖርም ስላላለ አጀንዳችሁ አልሠራም ብለዋል። በሃይማኖት መምጣታችሁም አይሠራም ነው ያሉት።
በሃይማኖት ስም የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ የተወሰኑ ሰዎችን ይጎዳል እንጅ ለየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ነኝ ለሚል ቡድን አይጠቅምም ሲሉ ገልጸዋል። በሰላም መንገድ ብትሠሩ ይሻላልም ብለዋል።
ሠብሠብ ብለን ሀገር እናልማ፣ እናንተ አንድ እርምጃ ስታስቡ 20 እጥፍ የሚያስብ መንግሥት ነው ያለው ብለዋል። ታጣቂዎች ወደ ሕግ እና ሥርዓት ብትመለሱ ይሻላልም ነው ያሉት።
በያየህ ፈንቴ
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
