
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር እሳቤ በበርካታ ቋንቋዎች እየተተረጎመ እና ከምሁራን ጋር ሰፋ ያለ ውይይት እየተደረገበት መኾኑንም አንስተዋል። የዚህ እሳቤ ጥልቅ ፍልስፍና የሰውን ህልውና በሚደግፉ ሦሥት መሠረታዊ ምሶሶዎች መካከል ጤናማ ሚዛን መፍጠር ላይ የተመሠረተ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሰው ልጅ ከተፈጥሮ እና ከፈጣሪ ጋር ያለውን ትስስር እና ሚዛን ካልጠበቀ ሕይወት እንደምትዛባ እና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የማይኖር እና የሕይወት ሥር ያልሰደደ ሰው ደግሞ የሰላም እና የልማት እንቅፋት ሊኾን እንደሚችል አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ተግባር ላይ ውሎ ውጤት ያስመዘገበው ይህ ሀሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃም በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጎመ መጠቀም እንደሚቻል እምነት እየተያዘበት መምጣቱን ጠቁመዋል። ሙሉ ፍልስፍና በመኾኑም ለሚቀጥለው ትውልድ ሰፊ ስንቅ ኾኖ እንደሚያገለግል፣ በተለይም ግለሰቦች በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።
✍️ ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_17_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
