
7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ታሪክ ጠገብ ሀገር ናት፤ ጠንካራ ሀገር ናት። በዚህ ጥንካሬዋ ምክንያት ባሕሏን፣ ማንነቷን፣ ሀገራዊ ስያሜዋን ይዛ ለዘመናት መዝለቅ የቻለችው ግን ከፈተና እና ከወጀብ ውጭ አልነበረም ብለዋል።
በርካታ ፈተናዎች በግራም በቀኝም ቢያጋጥማትም የተዘጋጀ ሕዝብ እና የተደራጀ ሠራዊት ያላት በመኾኑ እንደ ሀገር ለመጽናት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።
ይሄ ትልቅነት እና ታሪክ ግን በነጻ የመጣ ሳይኾን መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን በነጻ ሊገብሩ የፈቀዱ እና የወደዱ አባቶች እና እናቶች ስለነበሩ ነው ብለዋል።
ዛሬ በአፍሪካ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር እያልን ዓድዋን የምናስታውሰው “ዓድዋ” በነጻ፣ በችሮታ እና በልመና የመጣ ሳይኾን ዋጋ ለመክፈል የወደዱ ጀግኖች ስለነበሩባት ነው ብለዋል።
”ይሄ በየዘመኑ ሁሉ የሚቀጥል የእኔ እና የእናንተ ኀላፊነት በመኾኑ ይህንን ታሪክ እና ክብር ማስጠበቅ፣ ማስቀጠል እና ነጻነታችን ላይ የማንደራደር መኾን አለብን” ብለዋል።
ክላሽ ተሸክሞ 30 እና 40 ኪሎሜትር በዝናብ፣ በውርጭ እና በፀሐይ የሚጓዘውን ሠራዊት ማክበር እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ሌላው መሞት የለበትም በሚል ሌላውን ለማዳን ፈቅዶ የተሰዋን ሠራዊት ማክበር ይገባልም ነው ያሉት።
መከላከያ ሠራዊት በአንድ ምሶሶ ግንባታ አይቆምም። የሚጠበቅበትን ውጤትም አያመጣም። በዚህም መከላከያ የሚገነባበት ስትራቴጂ የአየር፣ የምድር እና የባሕር ኀይሉን ያቀፈ መኾን አለበት ብለዋል።
ከሚገነባበት አቅጣጫዎች አንደኛው ራስን መቻል ስላለበት ሠራዊቱ ዛሬ የራሱን ምግብ፣ የራሱን ልብስ፣ የራሱን ትጥቅ በበቂ ማምረት የሚችል ተቋም ኾኗል ብለዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ሠራዊቱ ቴክኖሎጂን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀም ተቋም እንዲኾን ታልሞ እየተገነባ እንደኾነም ጠቁመዋል።
በሦሥተኛ ደረጃ የብዙ አፍሪካ ሀገራትን ጭምር የተለያዩ ሥልጠና መስጠት የሚችል አቅም እየገነባ ይገኛል ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት መከላከያ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የትጥቅ ምርት ኤክስፖርት አድርጓል። ጥይት፣ ድሮን እና የአውሮፕላን ጥገናዎች ከፍተኛ ገቢ ማስገባት ችለዋል። ራሱን እየደገፈ አምራች እየኾነ የሚሄድበትን መንገድ ለመከተል ተሞክሯል ነው ያሉት።
መከላከያው መጀመሪያ የሚጠበቅበት ጂኦፖለቲክስን ቀድሞ የማወቅ እና የመለየት አቅም መፍጠር፣ ግጭትን እና ጉዳትን ማስቀረት፣ ከዚያም አልፎ ሲመጣ መከላከል መቻል አለበት ብለዋል።
በቴዎድሮስ ደሴ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
