
7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ.ር) ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ከተሞች የሀብት ምንጭ ኾነዋል፤ የኮሪደር ልማት ያስገኘውን ውጤት የተረዱት የአፍሪካ ሀገራት እንኳ የኮሪደር ልማትን ለመተግበር ልምድ እንድናካፍላቸው ጥያቄ ያነሳሉ ብለዋል። ኮሪደር ልማት ሰዎችን ለማፈናቀል የሚሠራ አይደለምም ነው ያሉት። የሚሠሩ ሥራዎችን ከማራከስ አብሮ መሥራት ለሀገር ይጠቅማልም ብለዋል።
122 የመሶብ አገልግሎት ተደራሽ መኾኑንም ተናግረዋል። በሞባይል አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑንም ጠቁመዋል። ዲጂታል ሥርዓትን ለመገንባት መሠራቱንም ገልጸዋል። ከ10 በላይ አነስተኛ የውኃ ግድቦች መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል።
ቆላማ አካባቢዎች ላይ በፍጥነት የሚደርሱ አዳዲስ የምርት ዝርያዎችን ለማምጣት፣ መኖ በስፋት በማምረት ማከማቸት ላይ በትኩረት በመሥራት ኤሊኖ ያደርሳል የተባለውን ጉዳት በቂ ዝግጅት በማድረጋችን አንድ በመቶ ያክል እንኳን ጫና ሳይፈጥር አልፏል ነው ያሉት።
የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የዝናብ እጥረት አጋጥሞ እንደነበረም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሠራነው የሪፎርም ለውጥ ከነበረበት ሥብራት ቀና ማለት ችሏል ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር በአንድ ጀምበር የሚፈታ አይደለም ነው ያሉት።
ከነበርንበት አረንቋ ወጥተናል፣ ጉዞችን ትክክለኛ መኾኑን አውቀናል፤ ብዙ ጥረት፣ ድካም እና ትብብር ያስፈልጋል ይህን ስናደርግ ማደግ እንችላለን ነው ያሉት።
በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ከስሀራ በታች ሦሥተኛ የኾነው ኢኮኖሚያችን በቀጣይ አምስት ዓመት ደግሞ ደረጃውን ከፍ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም ብለዋል።
በያየህ ፈንቴ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
