
7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ከኤክስፖርት አኳያ ባለፉት ሦሥት ወራት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ይህ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ25 በመቶው በላይ ዕድገት አለው። 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ የሦሥት ወር ኤክስፖርት ሳይኾን የዓመት ኤክስፖርት ነበር ነው ያሉት።
ከአገልግሎት አንጻር ባለፉት ሦሥት ወራት 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ማግኝት ተችሏል፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 27 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ባለፉት ሦሥት ወራት 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 34 በመቶው እድገት አለው ነው ያሉት።
አጠቃላይ በኤክስፖርት፣ በሰርቪስ፣ በውጭ ዳይሬክት ኢንቨስትመንት፣ በሐዋላ በልዩ ልዩ የሚገኙ ገቢዎች ካለፉት ዓመታት ከምናውቀው ገቢ ከፍ ያለ መኾኑን ጠቁመዋል።
ኢምፖርትን በሚመለከት ባለፉት ስድስት ወራት 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያክል ወጪ ወጥቷል። በዚህም ውስጥ የነዳጅ ድርሻ ከባለፈው ዓመት 70 በመቶው ብልጫ አሳይቷል። በተለያዩ ምክንያቶች ለነዳጅ የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛ ኾኗል ነው ያሉት።
በቂ የነዳጅ ዲፖ የሌላት ሀገር ነዳጅን መደጎም ብቻ ሳይኾን አብቃቅቶ መጠቀም መቻሉ በከፍተኛ ደረጃ ምሥጋና ሊቸረው የሚገባ ተግባር ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
ወደብ የሌላት ሀገር ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ሀገራት ጋር ስትወዳደር በጣም ዝቅተኛ በኾነ ዋጋ ነዳጅ የምታቀርብ ሀገር ስለመኾኗም ጠቁመዋል።
እንደ ምሳሌ ለማንሳት ኬንያን ለአንድ ሊትር ነዳጅ 1ነጥብ 7 ዶላር፣ ጅቡቲ 1ነጥብ 77 ዶላር በሊትር፣ ዩጋንዳ 1ነጥብ 57 ዶላር፣ ታንዛንያ 1ነጥብ 53 ዶላር እና ሩዋንዳ 1ነጥብ 99 ዶላር በሊትር እንደሚያወጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአንድ ሊትር ነዳጅ 1ነጥብ 04 ዶላር እንደምታወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል። ይህም በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ሀገራት በሙሉ ሲታይ በጣም ዝቅተኛው ነው ብለዋል።
በተደረገው ድጎማም የነዳጅ ተቋሙ ባለፉት ስድስት እና ሰባት ወራት ወደ 480 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ እዳ ተሸክሟል ነው ያሉት።
በአንድ ሊትር 90 ብር እየደጎሙ ማስቀጠል አስቸጋሪ በመኾኑ እየታየ ማሻሻያዎች ይደረጋሉም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
