ከኪሳራ ወጥቶ 43 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስገኘው የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን።

22

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጂኦፖለቲካ ውጥረቶች፣ ግጭቶች እና የንግድ መስመሮች መታወክ በፈጠሯቸው ተግዳሮቶች መካከል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አመርቂ ለውጦችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ለ11 ዓመታት ያልተደረገ የኢኮኖሚ ክለሳ እና ሰፊ የሴንሰስ ሥራ በስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ተከናውኖ፣ ቀደም ሲል በሂሳብ ያልተካተቱ አዳዲስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለመለካት አስችሏል ነው ያሉት።

ዲጂታል ኢኮኖሚው በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ደረጃ መድረሱ፣ የከተማ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች መሠረተ ልማትን ማስፋፋታቸው፣ የግብርና ክላስተር እና የሌማት ትሩፋት መጎልበታቸው ተጠቅሷል።

ከለውጡ በፊት ሦሥት ብቻ የነበሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን ከ15 በላይ መድረሳቸው፣ የአረንጓዴ እና የኢነርጂ አቅም ማደጉ፣ በአንድ ቀን ሁለት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማስተናገድ የሚያስችል የቱሪዝም አቅም መገንባቱንም አመላክተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም በአፍሪካ ከፍተኛ አፈጻጸም አሳይቷል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን በሪፎርም አሠራር በመመራቱ ከቀድሞው አነስተኛ ትርፍ በዘለለ 43 ቢሊዮን ብር ትርፍ የሚያስገኝ ኾኗል ብለዋል። ሎኮሞቲቮች ከ11 ወደ 36፣ ጋሪዎች ከ1 ሺህ በላይ አድገዋል።

መንገደኛ በማጓጓዝ ከ198 ሺህ ወደ 588 ሺህ ማሳደግ ተችሏል። የቡና ኤክስፖርት ቢያንስ 95 በመቶ እና የማዳበሪያ ኢምፖርት 25 በመቶ በባቡር እየተጓጓዘ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በመጨረሻም በተሠራው ጥናት መሠረት የኢትዮጵያ ጂዲፒ 210 ቢሊዮን ዶላር ኾኗል፤ ይህ ውጤት ኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ከደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ቀጥሎ ሦሥተኛዋ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር አድርጓታል ብለዋል።

✍️ ስማቸው አጥናፍ

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_17_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article‎”የኢትዮጵያ ዋና ግብር ከፋይ የመንግሥት ኩባንያዎች ናቸው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article#አንኳር