
7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ሥብሠባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል። በስብሰባው ላይ የምክር ቤት አባላት በብሔራዊ ደኅንነት፣ በሰላም፣ በልማት ፕሮጀክቶች፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ አገልግሎቶች ዙሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ከብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት ጋር በተያያዘ ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል፣ የግብጽን ተልዕኮ ተቀብለው የሚሠሩ ባንዳዎችን በሀገር ክህደት ወንጀል የሚያስጠይቅ የሕግ ማዕቀፍ እና ድንጋጌ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል። እነዚህ አካላት የውጭ ኀይሎችን ሴራ ተረድተው የኢትዮጵያን ጸጋዎች እንዲያውቁ በዘላቂነት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያን ማንሠራራት ለማስቆም የሚሠሩ ታሪካዊ ጠላቶችን ለመመከት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በቴክኖሎጂ እና በሌሎች አቅሞች ይበልጥ ለማጠናከር የተያዘው ዕቅድ እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል።
በውጭ ግንኙነት እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ረገድም፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት እየተደረገ ያለው ጥረት የደረሰበት ደረጃ፣ ሀገሪቱ ለቀጣናው መረጋጋት የምትጫወተው የመሪነት ሚና እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አሁን ያለበት ሁኔታ እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል።
በተለያዩ ክልሎች የሚታዩ ዘረፋዎች፣ የመንገድ መዘጋት እና የንጹሐን ሞት እንዲቆም መንግሥት ውስጡን ፈትሾ አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ነው የምክር ቤት አባላት የጠየቁት።
ከትግራይ ክልል አኳያ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ሕዝቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ ምን እንደኾነ እንዲብራራላቸውም ነው የጠቆሙት።
የሕዝብ ቅሬታ የኾነውን ሙስና እና ብልሹ አሠራር ለመግታት ጠንካራ እና አስተማሪ የሕግ እርምጃ ለመውሰድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት እና በማኅበራዊ ዘርፎችም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና የጉባ ብሥራት ሜጋ ፕሮጀክቶች ወቅታዊ የግንባታ አፈጻጸም፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን እና ጥሬ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ለማሟላት የሚደረገው ጥረት የደረሰበት ደረጃንም ጠይቀዋል።
ከኑሮ ውድነት እና ከነዳጅ ድጎማ አንጻር የነዳጅ ድጎማ ኢኮኖሚውን ሳይጎዳ ለምን ያህል ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ምን እንደኾኑም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ነው የጠየቁት።
በመድኃኒት አቅርቦት ላይ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባራትን፣ የሕክምና መሣሪያዎች ብልሽትን እና የሙያ ሥነ ምግባር ክፍተቶችን ለመቅረፍ የተያዘው ዕቅድ፤ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የመምህራንን ኑሮ ማሻሻል እና ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነት፤ እንዲሁም ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው ሦሥተኛው የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መቼ እንደሚካሄድ እንዲገለጽ ተጠይቋል።
በያየህ ፈንቴ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
