
ዓለም ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየተመለከተች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በመጪው 2027 ታላቁን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) የማስተናገድ ዕድል አግኝታለች።
የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ይህ መድረክ ሀገራችን በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን የመደራደር አቅም እንድታሳድግ ሰፊ በር ይከፍታል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ሐሳቡ ተስፋ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን በፕሬዝዳንትነት እንድትመራ እና እንድታስተናግድ መመረጧ የላቀ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ አንድምታ አለው።
ይህም በዓለም መድረክ የመደራደር አቅምን ከማጎልበት ባለፈ የአፍሪካን የጋራ አጀንዳ ለማስፈጸም እና ዲፕሎማሲያዊ ሚዛንን ለማስጠበቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ዓለም ዛሬ በተለዋዋጭ እና በማይገመት የኀይል አሰላለፍ ውስጥ ትገኛለች የሚሉት መምህር ሐሳቡ ቀደም ባለው ዘመን የሀገራት ጂኦ-ፖለቲካዊ ኀይል ይለካ የነበረው ባላቸው የተፈጥሮ ጋዝ ወይም የነዳጅ ክምችት ነበር ብለዋል።
አሁን ግን የጂኦ-ፖለቲካዊ ኀይል ሚዛን መለኪያዎች ከነዳጅ እና ከተፈጥሮ ጋዝ ወደ ታዳሽ ኀይል እየተቀየሩ መጥተዋል ነው ያሉት
ታዲያ ዓለም ትኩረቱን ወደ ታዳሽ ኀይል በቀየረበት በዚህ ወቅትም የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ እና የአረንጓዴ ሀብት ለሀገራት ሚዛን ማስጠበቂያነት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ኾኖ ብቅ ብሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሀብቶችን፣ ሳይንቲስቶችን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እና የቢዝነስ ተወካዮችን የሚያሳትፈው ኮፕ 32 ጉባኤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተሰሚነትን፣ ተአማኒነትን እና ቅቡልነትን እንድትጎናጸፍ ዕድል መኾኑንም የፖለቲካ ምሁሩ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ መድረኩን በፕሬዝዳንትነት መምራቷ የባሕር በር ጥያቄዋን እና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን በተመለከተ የሚገጥሟትን የዲፕሎማሲ ፈተናዎች እና ጫናዎች ለማቃለል፣ ብሔራዊ ጥቅሞቿ እንዲከበሩ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ ድምጽ የምታሠባሥብበት መድረክ ኾኖ እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል።
አፍሪካ በአየር ንብረት ብክለት ላይ የሚኖራት ሚና ዝቅተኛ ቢኾንም በአየር ንብረት ለውጥ በሚመጣው ጉዳት ግን በከፍተኛ ደረጃ የምትጠቃ አህጉር ናት።
በዚህ ምክንያት አፍሪካውያን ፍትሐዊ ካሳ እንዲያገኙ በተለያዩ ወቅቶች ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል። ኮፕ 32 በአፍሪካ መዲና በአዲስ አበባ መካሄዱ ለዚህ የካሳ ይገባኛል ጥያቄ እና ድርድር ምላሽ ለማግኘት የጎላ ፋይዳ እንዳለውም መምህሩ አመላክተዋል።
ይሁን እንጂ ይህንን ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ዕድል ወደ ዘላቂ ጥቅም ለመቀየር ቀጣናዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን በብቃት ማጠናከር እንደሚገባም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
