
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከስዊዲን፣ ከጀርመን እና ከደቡብ አፍሪካ የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ በመኾን ያዘጋጀው “5ኛው ምዕራፍ የቀንዱ ወግ” ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው “በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ትብብርን በአዲስ መልክ መቃኘት፤ ስትራቴጂካዊ መተማመንን፣ ቀጣናዊ የባለቤትነት ሚናን እና በትብብር ላይ የተመሠረተ የጋራ ተደጋጋፊነትን መገንባት” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግዛቸው አስራት (ዶ.ር) በአፍሪካ ቀንድ የንግድ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን መሠረት ያደረገው የውጭ ኀይሎች ፍላጎት በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ላይ ከባድ ጫና እንደሚያሳድር ተናግረዋል።
ቀጣናዊ ንግግር ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ ያነሱት ዶክተር ግዛቸው የአፍሪካ ቀንድን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም እና ቀጣናዊ ትስስር ለማጠናከር ያሉ ዕድሎችን ወደ መጠቀም መሸጋገር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህም ስትራቴጂካዊ መተማመን እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ትብብር አስፈላጊ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ደኅንነት ተቋም የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ፖል ሲሞን (ዶ.ር) በበኩላቸው ከዚህ በፊት መሰል ምክክሮች በተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካሄዳቸውን አንስተዋል።
በሀገራት መካከል መተማመን መፍጠር ውሥብሥብ በኾነ ዓለም ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ነው፤ ውጫዊ ኀይላት የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ፍላጎት በሚያንዣብቡበት አካባቢ መሰል ውይይቶች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።
ሀገራትም የቀጣናቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመወሰን አቅም ማዳበር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።እንዲህ ዓይነት መድረኮች ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለምሁራን እና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ወሳኝ መኺናቸውንም ዶክተር ፖል አክለዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዳም ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ቀጣናዊ ትብብር ችግሮችን ለመፍታት እጅግ ውድ ሀብት ነው ብለዋል።
በርካታ ፍላጎቶችን በሰላም ለማስተናገድ ተግባራዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማመንጨት መተማመንን መፍጠር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
ብዙ ፍላጎቶች በሚንጸባረቁበት በዚህ ቀጣና ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በሰላም እና በዲፕሎማሲ መንገድ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለቀጣናዊም ኾነ ለአህጉራዊ ትብብር ቁርጠኛ መኾኗን የጠቆሙት አቶ አዳም ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዲኖር በኢጋድ እና በአፍሪካ ኅብረት መርህ መሠረት እንደምትሠራ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለዚህ የሰላም ሥራ ለታሪኳ ብቻ የምትተወው ሳይኾን አሁንም ተግባራዊ እንቅስቃሴዋን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
የወደፊቱ የአፍሪካ ቀንድ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በቀንዱ ሀገራት ትብብር ነው ያሉት ደግሞ የኮንራድ አዴናወር ፋውንዴሽን (KAS) የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ውይይት ቀጣናዊ መርሐግብር ዳይሬክተር ጃን ኦሌ ናቸው።
ይህን ለማድረግ መቀራረብ፣ የጋራ ግንዛቤ መያዝ እና ፈጣን እና ተለዋዋጩን ዓለም ተገንዝቦ ውሳኔ ማሳለፍ ወሳኝ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
