
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው እና ከ127 ሀገራት፣ ከ46 ሺህ በላይ የአፍሪካ እና የዓለም የዘርፉ ተሣታፊዎች የተገኙበት 5ኛው ዓለም ዓቀፍ የአፍሪካ የኅብረተሰብ ጤና ጉባኤ ሦሥተኛ ቀኑን ይዟል።
ይህ ቁጥር ክብረ ወሰን ኾኖ መመዝገቡን የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል አፍሪካ (ሲዲሲ) ገልጿል።
ይህ ትልቅ አህጉራዊ ጉባኤ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት እና ክትባት ምርትን ማስፋፋት፣ ዲጂታል ጤና እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀም እንዲሁም የወረርሽኝ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዝግጁነትን ማጠናከር ላይ አተኩሯል።
በተለይ የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ላይ ከ2026 እስከ 2030 የሚተገበረው ፍኖተ ካርታ ይፋ የኾነበት ጉባኤ ነው።
እነዚህም የመጀመሪያው በቤት ውስጥ የሚደረጉ ወሊዶችን ዜሮ ማድረግ፣ ሁለተኛው መከላከል የሚቻሉ የእናቶች እና የጨቅላ ሕጻናት ሞትን ዜሮ ማድረግ፣ እንዲሁም ሦሥተኛው ክትባት ያላገኙ ሕፃናትን ዜሮ ማድረግ ናቸው።
የኢትዮጵያ የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ተሞክሮ ሌላኛው ነጥብ ሲኾን ኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክስ የጤና መዝገቦች፣ በማኅበረሰብ ዲጂታል ሥርዓቶች እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የገነባችውን አቅም ያሳየችበት ነው።
ርቀት እና የባለሙያ እጥረትን በቴክኖሎጂ በማለፍ በሩቅ አካባቢ ያሉ አዋላጆችን እና ሐኪሞችን ከስፔሻሊስቶች ጋር ማስተሳሰር እና የሕክምና ልኅቀት ማዕከላትን ማቋቋም ዋና ቅድሚያ የተሰጠው አህጉራዊ ጉዳይ ነው።
የውስጥ ፋይናንስ እና ተጠያቂነትን በተመለከተ ቢያንስ 15 በመቶ ብሔራዊ በጀት ለጤና የመመደብ የአቡጃ ግብ እንዲሳካ፣ የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲ እና የጋራ ግዥ ሥርዓት እንዲጠናከሩ፣ የእናቶች እና ሕጻናት ሞትን የመቀነስ ልምድ እንዲስፋፋ እና በአዋላጅነት እና ጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ልዩ የሥልጠና ዕድሎች እንዲመቻቹ ማድረግም ሌሎቹ ናቸው።
የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል የአሥር ዓመታት ጉዞ በሚታሰብበት በዚህ ጉባኤ፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የጤና አሥተዳደር ድምጿን በማሳደግ የራሷን የጤና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የምትወስዳቸው ተግባራዊ እርምጃዎች ዋነኛ ማሳያ ኾነዋል።
ዘጋቢ:- መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
