ከተበታተነ አቅም ወደ አንድ የማይበገር ኃይል

11

የአንድ ሀገር ሀብት የሚለካውና ብልፅግናዋ የሚሰፈረው በመሬቷ ውስጥ በተቀበረ ወርቅ ወይም በወንዞቿ ብዛት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም እነዚያን የተበታተኑ ጸጋዎች በአንድ ገመድ ቋጥሮ፣ በአንድ ዓላማ አሰልፎ ወደ ሀብት የመቀየር ጥበብ ሲኖር ነው።

ለዚህም ነው በተፈጥሮ ሀብት የበለፀጉ አንዳንድ ሀገራት አሁንም በድህነት ውስጥ ሲገኙ፣ የተወሰኑ ሀብቶች ብቻ ያሏቸው ሌሎች ሀገራት ግን በፈጠሩት የኢኮኖሚ አሠራር ምክንያት የተሻለ ዕድገት ማስመዝገብ የቻሉት።

ኢትዮጵያ በመሬት፣ በውሃ፣ በማዕድን፣ በታሪክ፣ በባሕልና በሰው ኃይል የበለፀገች ሀገር ብትሆንም፣ ለዘመናት የነበረው የልማት ጉዞዋ ግን እንደ ሀገሬው አባባል “አንድ እግር ላይ እንደቆመ ሰው” በአንድ የግብርና ዘርፍ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነበር። ሌሎቹ እምቅ አቅሞቿ ተበታትነው፣ ዘርፎችም በቂ ትስስር ሳይኖራቸው በተናጠል ሲጓዙ ቆይተዋል።

ግብርና ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ ለወጪ ንግድና ለሥራ ዕድል መፍጠር ያለው ሚና አይካድም። ይሁን እንጂ ከዝናብ ጥገኝነት ያልተላቀቀና ከሌሎች ዘርፎች ጋር በበቂ ሁኔታ ያልተሳሰረ ግብርና፣ በድርቅም ሆነ በጎርፍ ሲፈተን ኢኮኖሚውን በቀላሉ ለተጋላጭነት ይዳርጋል።

በተጨማሪም ጥሬ ዕቃዎችን በትንሽ እሴት ወደ ውጭ መላክና በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ አለማቀነባበር፣ እንዲሁም የተቀነባበሩ ውድ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በማባባስ የሥራ ዕድል ፈጠራንና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን አዘግይቷል።

ዛሬ ይህንን የተበታተነ ጉልበት ሰብስቦ ወደ አንድ የማይበገር ኢኮኖሚያዊ ኃይል ለመቀየር፣ የመደመር ስትራቴጂ እና ባለብዙ የኢኮኖሚ ዘርፍ አካሄድ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ መልክ እየቀየሩ ይገኛሉ።

🇪🇹የተበታተነ አቅምን የሚሰበስበው የመደመር ጥበብ፦”መደመር” በኢኮኖሚ ቋንቋ ሲተረጎም ያለንን ሳንጥል፣ የጎደለንን እየሞላን፣ የተበታተኑ አቅሞችን በማቀናጀት ከድምር ውጤት በላይ የሆነ ስኬት (Synergy) የመፍጠር ስልት ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በዘርፎች መካከል የነበረው የአሠራር «ግንብ» ሀገሪቱ ያላትን ሙሉ አቅም እንዳትጠቀም አግዷት ነበር። የመደመር ስትራቴጂ ይህንን ግንብ በማፍረስ፦

የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም ከግሉ ዘርፍ ፈጠራና ካፒታል ጋር፣ የሀገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር፣ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ደግሞ በአንድ የእሴት ሰንሰለት በማስተሳሰር የሀገሪቱን የተበታተነ ጉልበት ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲፈስ ያደርጋል።

🇪🇹 በአንድ እግር ከመቆም ወደ አምስት ጽኑ ምሰሶዎች፦ በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ዝናብ ሲጠፋ ወይም የዓለም ገበያ ሲዋዥቅ በቀላሉ ይንገዳገዳል። ባለብዙ የኢኮኖሚ ዘርፍ ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ከዚህ ስጋት አውጥቶ በአምስት ጽኑ ምሰሶዎች ላይ እንድትቆም ያስችላታል፦

ግብርና (የሕልውናና የኢንዱስትሪ መሠረት)፦ ከዝናብ ጠባቂነትና ከባህላዊ አስተራረስ ተላቆ በመስኖ፣ በሜካናይዜሽንና በኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ማሳደግ፤ ይህም ዜጎችን ከመመገብ አልፎ ለፋብሪካዎች የማይነጥፍ ጥሬ ዕቃ ያቀርባል።

ማኑፋክቸሪንግ (የዕሴት ጭማሪና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ)፦ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማዳን፣ ጥሬ ዕቃዎችን ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ወጣቶችን የሥራ ባለቤት ማድረግ።

ቱሪዝም (የተፈጥሮና የታሪክ ጸጋን ወደ ሀብት መቀየር)፦ ለዘመናት ተረስተው የቆዩ የታሪክ፣ የባህልና የተፈጥሮ መስህቦችን በዘመናዊ መሠረተ ልማት አስውቦ (እንደ «ገበታ» ፕሮጀክቶች) ፈጣን የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት።

ማዕድን (በመሬት ውስጥ የተቀበረውን ሀብት ማውጣት)፦ ባህላዊ አሠራርን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተካትና ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን በመሳብ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ ማሳደግ።

ዲጂታል ኢኮኖሚ (የሁሉም ዘርፎች አፋጣኝ)፦ ፋይናንስን፣ ቴሌኮምንና ሎጂስቲክስን በማዘመን ለሌሎቹ አራት ዘርፎች ፍጥነት፣ ቅልጥፍናና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን መስጠት።

የመደጋገፍ ሰንሰለት፡ ዘላቂ ብልፅግና የሚወለድበት ሚስጥር የእነዚህ ዘርፎች ውበት የሚታየው ተነጣጥለው ሳይሆን ተሳስረው ሲሠሩ ነው። ግብርናው ሲዘምን ለማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ ይሰጣል፤ ፋብሪካዎቹ ሲያድጉ የትራንስፖርት፣ የባንክና የዲጂታል አገልግሎቶችን ያነቃቃሉ።

የቱሪዝም መዳረሻዎች ሲለሙ የአካባቢው አርሶ አደር ምርቱን የሚሸጥበት ትኩስ ገበያ ያገኛል፤ የዕደ-ጥበብና የአገልግሎት ዘርፉም ሕይወት ይዘራበታል። በዚህ የመደጋገፍ ሰንሰለት ውስጥ አንዱ ዘርፍ ሲያድግ ሌላውን እየጎተተ ያሳድገዋል።

ኢትዮጵያ የተበታተነ አቅሟን ሰብስባ ወደ ዘላቂ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ የምኞት ሳይሆን የስትራቴጂ ጉዳይ ነው። ባለብዙ የኢኮኖሚ ዘርፍ የሀገሪቱን የዕድገት ሜዳ ሲያሰፋ፣ የመደመር ስትራቴጂ ደግሞ በዚያ ሜዳ ላይ የሚጫወቱ ተዋናዮችን ሁሉ በአንድ ዓላማ ሥር አቀናጅቶ ድል እንዲቀዳጁ ያደርጋል። ጸጋዎቻችን ሲደመሩ፣ አቅሞቻችን ሲቀናጁ፣ ዘላቂ ብልፅግና የማይቀር እውነታ ይሆናል።

#የመደመር_መንግስት #ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

 

Previous article‎”የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ተሠርቷል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ያለመው የዓለም ዓቀፉ የአፍሪካ የኅብረተሰብ ጤና ጉባኤ።