
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የገቢ ትምህርት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ የገቢ አሠባሠብ ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢሮው በ2019 በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት ገቢ 166 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ አቅዶ እየሠራ ነው።
እስከ ኅዳር 14/2019 ዓ.ም ድረስ 41 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ ተችሏል። ይህም የዕቅዱ 24 ነጥብ 8 በመቶ ነው። ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው።
ለውጤቱ የክልሉ ነባራዊ ሁኔታ መሻሻል እና አዲሱን ቴክኖሎጂ ከመላመድ ጋር የተገናኘ እንደኾነ ጠቁመዋል።
በቅሬታ እና ይግባኝ አፈታት ሂደት እስካሁን ከቀረቡት 87 ሺህ 903 የግብር ከፋዮች ቅሬታዎች ውስጥ 84 ሺህ 932 የሚኾኑት ምላሽ አግኝተዋል፤ ቀሪዎቹንም በፍጥነት በማየት የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ይገባል ነው ያሉት።
ለክልሉ ትልቁ ራስ ምታት የኾነው የይግባኝ ጉዳይ ከገቢ ተቋሙ ባለሙያዎች ውጪ በሌሎች አካላት የሚታይ በመኾኑ መገፋፋቶች እየታዩበት ይገኛል። እስካሁን ከቀረቡት 26 ሺህ 954 የይግባኝ ጥያቄዎች ውስጥ 16 ሺህ 470 የሚኾኑት ታይተዋል፤ ቀሪዎቹንም በየደረጃው ያሉ መሪዎች እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች በፍጥነት በመፍታት ነጋዴውን ማኅበረሰብ ከመጉላላት ሊታደጉት ይገባል ብለዋል።
በደረሰኝ አሰጣጥ ሕግ መተላለፍ ምክንያት በ2019 ዓ.ም እስከ ኀዳር 11/2019 ዓ.ም ድረስ 348 ግብር ከፋዮች 100 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
በክልላችን ያለው የደረሰኝ አሰጣጥ እና አቀባበል ሥርዓት የተዛባ በመኾኑ፣ ኅብረተሰቡ ደረሰኝ የመቀበል ልማድ እንዲኖረው ከማስተማር ጎን ለጎን ደረሰኝ የማይሰጡ አካላትን በመቅጣት እና የተጣለውንም ቅጣት በአግባቡ በማስከበር ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በተፈጸሙ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ምክንያት በ54 ሠራተኞች ላይ እስከ ሥራ ስንብት የሚደርስ ጥብቅ እርምጃ ተወስዷል።
አቶ ታዘባቸው ከገቢ አሠባሠብ ጋር በተገናኘ ያጋጠሙ ችግሮችን አንስተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነባራዊ ሁኔታዎች፣ ለቀረቡ ቅሬታዎች እና ይግባኞች ፈጣን ምላሽ አለመስጠትን በችግር አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ጅምላ ነጋዴዎች እንዲሁም የሲሚንቶ እና የብረታ ብረት ፋብሪካዎች ሕጋዊ ደረሰኝ ባለመስጠታቸው በቸርቻሪ ነጋዴዎች እና በክትትል ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እና ግጭት እየፈጠረ መኾኑ በችግርነት ተመላክቷል።
ዜጎች ሳይገዙባቸው በቲን ቁጥራቸው ብቻ ሌላ አካል ሕገ-ወጥ ግብይት በመፈጸሙ ንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና የሀብት ጫና በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ኾኖ ተመላክቷል።
በስማቸው አጥናፍ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
