
የጤና ሉዓላዊነት ማለት ሀገራት ከውጭ እርዳታ እና አቅርቦት ጥገኝነት ነጻ በመኾን የሕዝባቸውን ጤና የመጠበቅ፣ የማከም እና ፖሊሲዎቻቸውን በራሳቸው የመወሰን አቅም ማረጋገጥ ሲኾን በተለይ ለአፍሪካ የህልውና ጉዳይ ነው።
የአፍሪካ ጤና ሉዓላዊነት እውን እንዲኾን ደግሞ መዋቅራዊ ለውጥ አስፈላጊ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ5ኛው ዓለም ዓቀፍ የአፍሪካ የኀብረተሰብ ጤና ጉባኤ መክፈቻ ላይ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕክምና ልህቀት ማዕላትን መገንባት፣ የአፍሪካ አምራቾችን ለማብቃት በጋራ ግዥ መፈጸም፣ በታካሚዎች ጤና ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥብቅ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ዋና ምሶሶዎች ኾነው ሊሠራባቸው ይገባል ብለዋል።
የሕክምና ልህቀት ማዕከላትን መገንባት:- ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ታካሚዎች ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር በመጓዛቸው አፍሪካ በየዓመቱ ግምታዊ ዋጋው ሰባት ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣ ናይሮቢ የሚገኘው የአጋ ከን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
አፍሪካ በውጭ ሕክምና ሳቢያ የሚባክነውን ከፍተኛ የሀብት ፍሰት እና የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሕክምና ልህቀት ማዕላትን በሀገር ውስጥ መገንባት ይኖርባታል።
ይህ እርምጃ የውጭ ምንዛሪ ውጣ ውረድን ከማስቀረት እና የባለሙያዎችን ፍልሰት ከመግታት ባለፈ ለቀጣይ የጤና ምርምር አስተማማኝ መሠረት ይጥላል።
የአፍሪካ አምራቾችን ለማብቃት በጋራ ግዥ መፈጸም:- የአፍሪካ ሀገራት በውጭ ሀገራት የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች ጥገኝነት ምክንያት ለከፍተኛ የዋጋ ጫና እና የአቅርቦት ሰንሰለት ቀውስ የተጋለጡ ናቸው። ይህንን ተጋላጭነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማብቃት አህጉራዊ እና ዞናዊ የጋራ ግዥ ማዕቀፎችን መዘርጋት ወሳኝ መፍትሄ ነው።
የጋራ ግዥ ስልት ለሀገር ውስጥ አምራቾች ትልቅ ማበረታቻ በመኾን የፋርማሲዩቲካል ምርትን በማሳደግ፣ መድኃኒቶች በታለመላቸው ዋጋ እንዲገኙ በማድረግ እና አፍሪካ በድንገተኛ አደጋዎች ጊዜ በራሷ አቅርቦት ላይ እንድትተማመን ያስችላታል።
በታካሚዎች ጤና ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥብቅ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ:- በጤናው ዘርፍ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት መዋቅራዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገቶች ብቻቸውን በቂ አይደሉም፤ ስኬታቸው የተመሠረተው ግልጽነት ባለው አሥተዳደር፣ በታካሚዎች አገልግሎት ጥራት፣ ስህተቶችን በመቀነስ እና በባለሙያዎች ጥብቅ የሥነ-ምግባር አፈጻጸም ላይ ነው።
የሀብት መመደብ ብቻውን በቂ ባለመኾኑ አገልግሎቱ በሰብአዊነት እንዲሰጥ እና የሕዝብ ገንዘብ በአግባቡ እንዲመራ ጥብቅ የቁጥጥር፣ የክትትል ሥርዓቶች እና የሕግ ማዕቀፎችን መዘርጋት ለጤና ሉዓላዊነት እውን መኾን የማዕዘን ድንጋይ ናቸው።
በአጠቃላይ የአፍሪካ ጠንካራ የጤና ሥርዓት እውን የሚኾነው እነዚህ ሦሥት መሠረታዊ ምሰሶዎች በቁርጠኝነት ሲተገበሩ ብቻ ነው።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
#የመደመር_መንግሥት!
#Ameco #Medical_Excellence #Local_Manufacturing #Health_Equity #Africa_Health_Sovereignty
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
