
”አየር ኃይላችን መመኪያችን” በሚል 2ኛው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ነው በቢሾፍቱ የሚካሄደው።
የኢፌዴሪ አየር ኀይል የተመሠረተበትን 91ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል “በድል እና መስዋዕትነት የደመቀ የኢትዮጵያ ሰማይ አለኝታ” በሚል መሪ መልዕክት ከኅዳር 18/2019 ዓ.ም እስከ ኅዳር/21 2019 ዓ.ም ይከበራል።
የዚህ መርሐ ግብር አካል የኾነውን 2ኛውን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አስመልክቶ አየር ኀይሉ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢፌዴሪ አየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ኀይሉ የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር ጎን ለጎን ተቋማዊ እና ሀገራዊ ልማትን እያከናወነ የሚገኝ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል።
አክለውም ተቋሙ የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ እና ይህ የጎዳና ላይ ሩጫም የዚሁ ጥረት አካል መኾኑን ተናግረዋል።
ሩጫው የአየር ኀይሉ ብራንድ መኾኑን ገልጸው የአካባቢው ሕዝብም በዚህ ስፖርታዊ ውድድር ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
እሑድ ኅዳር 20/2019 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በሚካሄደው በዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ800 በላይ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ከ10 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ።
ውድድሩ አየር ኀይሉ ለሀገር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚታወስበት እና የሀገር ሉዓላዊነት በአደባባይ የሚገለጽበት መድረክ መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉዑሽ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
