‎የዓለም አቀፍ መድረኮች መዳረሻ እና የጋራ ብልጽግናን እየገነባች ያለችው ኢትዮጵያ!

18

‎ኢትዮጵያ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ የምታሠባሥብ እንዲሁም የጋራ ርዕይን ወደ ተጨባጭ ልማት የምትቀይር የቀጣናው ብሎም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መነኻሪያ ለመኾን የሚያስችላትን ቁመና ከወዲሁ እየገነባች ትገኛለች።

‎‎በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እየተንጸባረቀ ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ በላቀ ዲፕሎማሲያዊ ቁርጠኝነት፣ በጋራ የልማት ተጠቃሚነት እና በዘርፈ ብዙ የትብብር ማዕቀፎች ላይ የተመሠረተ ነው።

‎‎የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የፓን-አፍሪካኒዝም መሪነቷን በዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በማደስ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች የጋራ መፍትሔ የሚፈልግ የውይይት እና የትብብር መድረክ ኾና እያገለገለች መኾኗን መግለጻቸው ይታወሳል።

‎‎ፕሬዝዳንቱ ሀገሪቱ ያላትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እና የዲፕሎማሲ አቅም በመጠቀም ሀገራትን በአንድ ጥላ ሥር በማሠባሠብ የጋራ ራዕዮችን ወደ ተግባራዊ የልማት ውጤቶች ለመቀየር የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለች መኾኗንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

‎‎ለዚህ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተጨባጭ ማሳያ የሚኾኑ በርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ክንውኖች መካከል የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮፕ (COP) ጉባኤ ተጠቃሽ ነው።

‎‎በኮፕ 31 ላይ ኢትዮጵያ ያደረገችው ንቁ ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ የአፍሪካን የአየር ንብረት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማስተጋባት እና እ.ኤ.አ. በ2027 በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የኮፕ 32 ዓለም አቀፍ ጉባኤ መሠረት ለመጣል እንደ ስትራቴጂካዊ መድረክ ጥቅም ላይ ውሏል።

‎‎በተመሳሳይ መልኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ትስስር እና የልማት ዲፕሎማሲ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ዘርፈ ብዙ ትብብርን እያጠናከረ መኾኑን አንስተዋል።

‎‎በመሠረተ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በንግድ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተቀረጹ የትብብር ማዕቀፎች ኢትዮጵያን የቀጣናው የኢኮኖሚ እና የልማት መነኻሪያ የሚያደርጉ ናቸው።

‎‎የተነደፉ የጋራ ዕቅዶች በተጨባጭ መሬት ላይ ወርደው ለሕዝቦች ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲውሉ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

‎‎ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታደርጋቸው የኀይል ሽያጭ ስምምነቶች እና የኤሌክሪክ ኀይልን ወደ ጎረቤት ሀገራት ማስተላለፏ የቀጣናውን የኢነርጂ ደኅንነት እና የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች ናቸው።

‎‎የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ የታዳሽ ኀይል መስፋፋት እና የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመተካት ርምጃዎች ኢትዮጵያ ለዓለም የምታካፍላቸው የልምዶች መሠረቶች ናቸው።

‎‎በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የCPHIA 2026 ጉባኤ ከ30 ሺ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበትና የሀገራችንን የማስተናገድ አቅምና ተመራጭነት የሚያረጋግጥ ነው።

‎‎በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ አካሄድ ሀገሪቱን የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና የትብብር ውይይቶች ዋነኛ መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ በቀጣናው ሰላም፣ መረጋጋት እና የጋራ ልማት እንዲረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።

‎‎ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

‎‎#የመደመር_መንግሥት!

‎‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

‎‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_15_2019_ዓ_ም

‎‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous articleምክር ቤቱ በመጪው ሀሙስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ጉባኤውን ያካሂዳል።
Next article‎የኢፌዴሪ አየር ኀይል 91ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የጎዳና ላይ ሩጫ ሊካሄድ ነው።