
ለ11 ዓመታት ያህል ሥር በሰደደ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር የቆየችው የእንጅባራ ከተማ፣ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነባው የቸውሳ ሐና ማርያም የውኃ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ከኅዳር 13/2019 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የከተማዋ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ገቢ አሠባሣቢ ኮሚቴ ሠብሣቢ አለበል በቀለ ሕዝቡ ንጽህናው ያልተጠበቀ የምንጭ ውኃ በመጠቀም ለጤና ችግሮች ሲጋለጥ መቆየቱን ገልጸዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሕዝብ የተመረጡ 12 ኮሚቴዎች ተደራጅተው ወደ ሥራ በመግባታቸው፣ ማኅበረሰቡ በጥሬ ገንዘብ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የክልሉ መንግሥት ወደ 56 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ የኤሌክትሪክ ክፍያ መፈጸማቸውን ነግረውናል።
የቁጥጥር ኮሚቴ አባል አቶ ጥላሁን ምህረትም ችግሩን ለመፍታት እስከ ፌዴራል ውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ድረስ በመሄድ እና ከከተማው ውኃ ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት ሥራውን በባለቤትነት ማከናወናቸውን ገልጸው፣ እየጨመረ ለመጣው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር በቀጣይም በትልቁ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የእንጅባራ ከተማ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ዘላለም ዘውዱ፣ በ2012 ዓ.ም ተጀምሮ ተቋርጦ የነበረው እና ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም በሕዝብ ኮሚቴ ዳግም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት የከተማዋን የውኃ ችግር ከ75 በመቶ በላይ እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።
ለግንባታው የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ከ75 በመቶ በላይ ድርሻ የወሰደ ሲኾን፣ ሕዝቡም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት ቁፋሮ አስተዋጽኦ በማድረግ በድምሩ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ውኃውን ለ24 ሰዓት ማዳረስ የሶላር ኀይልን ለመጠቀም እና ተጨማሪ የውኃ አማራጮችን ለማጥናት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አክለዋል።
በተያያዘ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ፣ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ሲያብራሩ እንዳሉት ከንጹህ መጠጥ ውኃ ጋር በተያያዘ የክልሉን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ሽፋን ወደ 79 ነጥብ 91 በመቶ ማሳደግ መቻሉን እና 91 የውኃ ተቋማትን ወደ ሶላር ኀይል ማሸጋገር ስለመቻሉ መግለጻቸው ይታወሳል።
ዘጋቢ፡- ሰለሞን ስንታየሁ
#የመደመር_መንግሥት!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
