
በአምስተኛው የአፍሪካ ኅብረተሰብ ጤና ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ የጤና አሥተዳደር የኢንቨስትመንት መሠረት መኾኑን ጠቅሰው አፍሪካ በሕክምና ልህቀት፣ በጋራ መድኃኒት ግዥ እና በተጠያቂነት ላይ በማተኮር የጤና ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የማኅበረሰብ ጤና እና የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅም የሕዝብ ጤና ጥበቃ በንጹሕ ውኃ፣ በተመጣጠነ ምግብ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንደሚጀምር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የበሽታ ስርጭት ስጋትን እንደሚቀርጽ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ እና አብዛኛዎቹ ሴቶች የኾኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መሠረታዊ አገልግሎትን እስከ እያንዳንዱ ቤተሰብ እያደረሱ መኾኑን አንስተዋል። የጤና ተቋማት በባለሙያ፣ በግብዓት እና በላቦራቶሪ መጠናከር እንዳለባቸው እና የታካሚ ሕክምና የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ስላበቃ ብቻ ሊቋረጥ እንደማይገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች መድኃኒቶችን በብዛት ለማምረት እየተሠራ መኾኑን እና ባለፈው ዓመት የተገኘው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የማቹሪቲ ደረጃ 3 ዕውቅና ጠንካራ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሩቅ ወረዳዎች ያሉ ባለሙያዎች ከስፔሻሊስቶች ጋር እንዲመካከሩ እና የታካሚ መረጃዎች በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲዘዋወሩ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት አመላክተዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና ዲጂታል ጤና የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሩ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) እና ዲጂታል ጤናን ለማሳደግ ኀላፊነት እንደሰጣቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ይህንን እንደሚመራ ገልጸዋል።
ዲጂታል የጤና መሣሪያዎች በአፍሪካውያን ተመራማሪዎች ተቀርጸው በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እና ሁኔታዎች መሥራት እንዳለባቸው እና የጤና መረጃዎችም በራስ ደንቦች መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ የጤና ተቋማት ጋር የጋራ ጥናት ያካሂዳልም ነው ያሉት። «መደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ» ከመላው አፍሪካ የሚመጡ ተማሪዎችን በመቀበል ሥልጠና እና ምርምርን እንደሚያሰፋም ጠቁመዋል።
ለወጣት ሳይንቲስቶችም ላቦራቶሪዎች፣ የምርምር በጀት እና የሥራ ዕድሎች ሊመቻቹላቸው ይገባል ብለዋል።
የ«መደመር» ፍልስፍና የተቋማትን ጥረት ማቀናጀት እንደሚጠይቅ እና በአንድ ሀገር ያለ ላቦራቶሪ የሌሎችን የበሽታ ልየታ ሊያግዝ እንደሚችል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዜጎች ልዩ ሕክምናን በቅርበት እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ጥራት ያላቸው አፍሪካዊ መድኃኒቶች እና ለጤና ምርቶች አስተማማኝ የጅምላ ገበያ በመፍጠር አምራቾችን ማበረታታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ኀላፊነትን፣ የፋይናንስ ምንጭን እና የግምገማ ጊዜን ግልጽ በማድረግ ውጤቱን በሕዝቡ የእንክብካቤ መሻሻል መለካት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመጨረሻም ዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፋቸውን ከአፍሪካ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር እንዲያጣጥሙ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ በኮፕ32 ጉባኤ ዓለምን ወደ አዲስ አበባ እንደምትቀበል ገልጸው፣ የአየር ንብረት ውሳኔዎች በማስረጃ እና በልምድ እንዲደገፉ አጋሮች ወደ ከተማዋ ዳግም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!