
በአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል አዘጋጅነት በአዲስ አበባ መካሄድ በጀመረው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ኅብረተሰብ ጤና ጉባኤ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሦስቱ ሀገራት መሪዎች ተወካዮች ፤ የአፍሪካን የጤና አገልግሎት፣ የንፅህና መሰረተ ልማት፣ ብቁ የሰው ኃይል ሥልጠና እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለማሳደግ በትብብር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሩሲያ ፌዴሬሽን ስቴት ሴክሬታሪ እና ምክትል የጤና ሚኒስትር ዶክተር ኦሌግ ሳላጋይ የሩሲያ ፌዴሬሽን እስከ 2029 በተራዘመው የትብብር ማዕቀፍ መሠረት የጋራ ሳይንሳዊ ምርምሮችን እና ተግባራዊ ልምምዶችን አጠናክራ እንደምትቀጥል ግልጸዋል።
ሩሲያ በአፍሪካ የሚከሰቱ አደገኛ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪዎችን፣ ልዩ ባለሙያዎችን፣ ከፍተኛ የመድኃኒት ጭነቶችንና የመከላከያ መሣሪያዎችን እንደምታቀርብ የገለጹ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወደ 10 ሺ 000 የሚጠጉ ተማሪዎች በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች እና ክሊኒኮች የሕክምና ሥልጠና እና ምርምር እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን፣ የአፍሪካ መሪዎች ለአህጉሪቱ የጤና ደኅንነት ያስቀመጡትን ግልጽ አቅጣጫ በተግባር ለመደገፍ ዩኤኢ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ሀገሪቱ ከ2017 ጀምሮ ባቋቋመችው «Reaching the Last Mile Fund» አማካኝነት መከላከል የሚቻል አይነ ስውርነት እና ዘላቂ የአካል ጉዳትን የሚያስከትሉ ቸል የተባሉ ሐሩራማ በሽታዎችን ከአፍሪካ ለማጥፋት እየሠራች መሆኗንም አስታውሰዋል።
በተጨማሪም እያንዳንዷ እናት እና ሕፃን አስፈላጊውን እንክብካቤ አግኝተው በደስታ የሚኖሩበትን ሥርዓት መፍጠር የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል::
የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዮናስ ጋር ስቶሬ ሀገራቸው ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት መጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት አርጋግጠዋል።
አምስተኛው የአፍሪካ ኅብረተሰብ ጤና ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ አዲአ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር እየካሄደ ነው።
#የመደመር_መንግሥት!
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኀይለየሱስ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
