
የባሕር በር የሀገራትን ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ አቅም ለመገንባት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል። በታሪክ በተፈጠሩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ ታሥተዳድራቸው የነበሩ የባሕር በሮች ከቁጥጥሯ መውጣት ዛሬ ላይ የበይ ተመልካች እንድትኾን አድርጓታል።
በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩት የዲቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ መምህር እና ተመራማሪ ገመችስ መርሻ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ለዘመናት የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች አንስተዋል። አሰብ፣ አዱሊስ፣ ገምበዛ፣ ዘይላ እና ሌሎች ወደቦችን ታሥተዳድር ነበርም ይላሉ።
የባሕር በሯን ተጠቅማ ደኅንነቷን በማስጠበቅ፣ የውጭ ግንኙነቷን በማሳለጥ፣ ከባሕር የሚገኙ ገጸ በረከቶችን በመጠቀም እና ያለ ወደብ ክፍያ ግብዓቶችን በማጓጓዝ ተጠቃሚነት እንደነበራትም ተናግረዋል።
ወደ ሕንድ ውቅያኖስ፣ ወደ አውሮፖ እና ኢንዶኔዥያ የምታደርጋቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ የውጭ ግንኙነቶች፣ የቀጣናውን ደኅንነት ለማስጠበቅ የምታከናውናቸው ተግባራት ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ወሳኝ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
በታሪክ አጋጣሚ የባሕር በር ማጣቷ እና በጅቡቲ ወደብ ብቻ መጠቀሟ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጫና ማሳደሩንም ገልጸዋል።
ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ገንዘብ አሁን ላይ እየተሠሩ የሚገኙ “የጉባ ብሥራቶች” ፕሮጀክቶችን እንደ ኒውክለር ኀይል፣ በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና መሰል ፕሮጀክቶችን ወጭ የመሸፈን አቅም ይፈጥር እንደነበርም ነው ያስረዱት።
የባሕር በር ማጣት ወደ ውጭ በሚላኩ እና በሚገቡ ምርቶች ላይ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን በማስከተል፣ ምርቶች በጉዞ ላይ የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዲያልፍ በማድረግ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ተመራማሪው ጠቁመዋል።
የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ ለልማት በስፋት እንዳይገቡ፣ የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር፣ ከባሕር የሚገኙ ማዕድናት እና የዓሣ ምርት እንዳትጠቀም በማድረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው ብለዋል።
ጥናቶችን መሠረት በማድረግ የባሕር በር ማግኘት የሀገሪቱን ዕድገት 35 በመቶ የሚጨምር መኾኑንም ተናግረዋል። ምርቶች በወቅቱ እንዲመጡ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ የውጭ ባለሀብቶች በብዛት እንዲገቡ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲረጋገጥ፣ የቀጣናው የባሕር ደኅንነት እንዲጠበቅ የባሕር በር ማግኘት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተቀብሎታል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። በሀገር ጥቅም ላይ አንድ መኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሀገርን ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚያዘገየው የወደብ ኪራይን ማስቆም እና የባሕር በር ማግኘት ከትውልዱ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
