‎ኮፕ 32 – ወርቃማው የዲፕሎማሲ እና ኢንቨስትመንት ዕድል ለኢትዮጵያ!

4

‎የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ የኮፕ ጉባኤን የሚያስተናግዱ ሀገራት ገጽታቸውን እንደሚገነቡ፣ ኢንቨስትመንታቸውን እንደሚያነቃቁ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ እና ባለሀብቶችን ወደ ሀገራቸው የሚስቡበት ዕድል እንደሚያገኙ ያለፉት ጉባኤዎች ያሳያሉ።

‎‎የዓድዋ ድል ባለቤት፣ የአፍሪካዊያን የነጻነት ተምሳሌት፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት መሥራችነት የተሳተፈችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በአረንጓዴ ልማት የሠራችው ሥራ የኮፕ 32 ጉባኤን ለማስተናገድ እንድትመረጥ አስችሏታል።

‎‎እንደ ቻይና እና አሜሪካ የመሳሰሉ ትልልቅ ሀገራት እየተሳተፉበት የሚገኘው የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን ስታስተናግድ ደግሞ የበርካታ ሀገራትን ቀልብ በመሳብ ተመራጭ የኢንቨስትመንት ሀገር እንድትኾን ዕድል ይሰጣታል።

‎‎የአፍሪካ ድምጽ የኾነችው ኢትዮጵያ በጉባኤው በተሳተፈችባቸው ወቅቶች የአፍሪካ ሀገራትን ጥቅም በማስጠበቅ ፍትሐዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ እንዲቀርብ እና የድርቅ መቋቋም አቅም እንዲጎለብት ከፍተኛ ሚና እየተወጣች ትገኛለች።

‎‎ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ምቹ የንግድ ሥነ-ምኅዳር በመፍጠር፣ የመሬት እና የማምረቻ ቦታ አቅርቦትን በማሻሻል፣ አሥተማማኝ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦትን በማሳደግ፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን በማዘመን፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ኢትዮጵያ እየሠራች ነው።

‎‎ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን ስታስተናግድ በታዳሽ ኀይል፣ በመሠረተ ልማት፣ በማዕድን ሀብት፣ በምርት እና ምርታማነት፣ በማኑፋክቸሪንግ በቱሪዝም እና በሌሎች ዘርፎች ያሏትን አማራጮች በማሳየት ባለሀብቶችን ለመሳብ እና የኢንቨስትመንት አማራጮቿን ለማሳወቅ ዕድል ይፈጥራል።

‎‎በቱርክ እየተካሄደ በሚገኘው ኮፕ 31 ጉባኤ እየተሳተፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና በታዳሽ ኀይል ልማት ያከናወነቻቸውን ሥራዎች እያስተዋወቀች እንደምትገኝ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

‎‎በኮፕ 32 ጉባኤ የመፈጸም አቅሟን ለማሳየት፣ ዓለም አቀፍ ገጽታዋን ለመገንባት፣ የአረንጓዴ ኢንቨስትመንቷን ለማስተዋወቅ፣ ባለሀብቶችን ለመሳብ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጅት እያደረገችም ትገኛለች።

‎‎የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ጉባኤ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የቀጣዩ ኮፕ 32 ጉባኤ አስተናጋጅ በመኾኗ ኮፕ 31 ጉባኤ ላይ የተለያዩ ዓላማዋችን ለማሳካት እየሠራች ነው ብለዋል።

‎‎ኮፕ 32ን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ድርድርን በማድረግ መሠረት እና መደላድል ለመፍጠር፣ ከአጋር አካላት ጋር ጥሩ ግንኙነትን ለማዳበር፣ የዓለም ሀገራት ኮፕ 32ን በጉጉት እንዲጠብቁት ለማስቻል በኮፕ 31 እየተሠራ ነው ብለዋል። ጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ተግባር ለዓለም ለማሳወቅ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

‎‎የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ጉባኤው የኢትዮጵያን ሀብት የምናስተዋውቅበት፣ ኢንቨስትመንትን የምንስብበት እና አጋርነትን የምንፈጥርበት ነው ብለዋል።

‎‎#የመደመር_መንግሥት!

‎‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

‎‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_14_2019_ዓ_ም

‎✍️ በያየህ ፈንቴ

‎‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article‎የግብጽ ሴራ መክሰም እና የኢትዮጵያ እውነት መገለጥ
Next article5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ መካሄድ መጀረ