‎የግብጽ ሴራ መክሰም እና የኢትዮጵያ እውነት መገለጥ

2

🇪🇹‎የዓባይ ወንዝ የተፈጥሮ ስጦታ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት የተከፋፈለ ቢኾንም ግብጽ ግን ለዘመናት የያዘችው የቅኝ ግዛት መንፈስ እና “ብቸኛ የውኃ ባለቤት ነኝ” የሚለው ዕብሪተኛ አቋም የተፋሰሱን እውነታዎች ያዛባ በደል ነው። ግብጽ ዛሬም እያደረገችው ያለው የሴራ አካሄድ ቀድሞ በግብጽ የነበሩ የተለያዩ መንግሥታት ሲያደርጉት የኖሩት ነው።

‎‎ሀገሪቱ የዓባይን ውኃ እንደ ግል ንብረቷ በመቁጠር ከላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚነሱትን ማንኛውንም ፍትሐዊ የልማት ጥያቄዎች እንደ ሕልውና አደጋ ትመለከታለች። ምሁሩ ፕሮፌሰር አደም ካሚል የግብጽ ማኅበረሰብ ዓባይን እንደ ብቸኛ የፈጣሪ ስጦታ አድርጎ ከልጅነቱ ጀምሮ በባሕሉ እና በወጉ በመታነጹ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቱን ልትጠቀም መነሳቷ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን አስረድተዋል።

‎በታሪክ ሂደት ውስጥ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት እና የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት ሙሉ በሙሉ በመንፈግ በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ ኢ-ፍትሐዊ ስምምነቶችን እንደ ብቸኛ ሕግ በማወጅ ቀጣናውን በአንድ ወገን ቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

‎‎ግብጽ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን እንደ ጂኦፖለቲካዊ አሻንጉሊት በመቁጠር የራሷን ጥቅም ብቻ ለማስቀደም ስትል የሌሎችን የኢኮኖሚ ዕድገት እና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ጥረቶች በዲፕሎማሲ ማዕቀፍ፣ በኢኮኖሚ ጫና እና በድብቅ ሴራዎች ስታደናቅፍ መኖሯ የቆየ ፖሊሲዋ ነው።

ይህ አካሄድ የተፈጥሮ ሀብትን በፍትሐዊነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ከመጠቀም መርህ ጋር ፍጹም የሚጋጭ እና የቀጣናውን ሰላም የሚፈታተን አደገኛ የአሥተዳደር የበላይነት ፍላጎት ማሳያ ነው።

‎‎ዛሬ ላይ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ ያደረገችው የለውጥ እርምጃ እና የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ይህንን የዘመናት ቅኝ ግዛታዊ የበላይነት ትርክት የሰበረ፣ የሉዓላዊነት እና የእኩልነት ማረጋገጫ ታሪካዊ ምዕራፍ ኾኗል።

‎‎የግብጽ የዕብሪት ፖሊሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከሰመ እና የተፋሰሱ እውነተኛ ባለቤቶች የጋራ የባለቤትነት ስሜት እየተቀዳጁ መጥተዋል። ሀገሪቱ አሁንም ካላት የጥንታዊ አስተሳሰብ ባለመላቀቅ በየመድረኩ የምታሳየው የጥፋት እና የማደናቀፍ ሩጫ የአፍሪካን አንገት የሚያስደፋ እና የጋራ ዕድገትን የሚያሰናክል ነው።

‎‎እውነተኛው የዓባይ ፍትሕ የሚረጋገጠው የቅኝ ግዛት ውርስ የኾኑ ኢ-ፍትሐዊ ስምምነቶች ሙሉ በሙሉ ሲወገዱ እና ሁሉም የተፋሰስ ሀገራት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የተፈጥሮ ጸጋቸውን በፍትሐዊነት እና በኀላፊነት ስሜት መጠቀም ሲችሉ ብቻ ነው።

‎✍️ በስማቸው አጥናፍ

‎‎#የመደመር_መንግሥት!

‎‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

‎‎#Ameco ​#Abay #GERD #Regional_Cooperation #Sovereignty #Ethiopia

‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_13_2019_ዓ_ም

‎‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article
Next article‎ኮፕ 32 – ወርቃማው የዲፕሎማሲ እና ኢንቨስትመንት ዕድል ለኢትዮጵያ!