ከአረንጓዴ ዐሻራ እስከ ኮፕ 32 ፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ዓለም አቀፋዊ ምዕራፍ!

11

ከንግግር እና ከወረቀት ባለፈ ተግባርን ያስቀደመው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ ሀገራችን በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ያስመዘገበችውን ድል በግልጽ ያሳየ ታላቅ ሀገራዊ ስኬት ነው።

ዓላማው የደን ሽፋንን ማሳደግ፣ የደን መጨፍጨፍን መከላከል፣ የመሬት መራቆትን መቀልበስ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን መፍታት የሆነው ይህ መርሐ ግብር፤ ተጨባጭ በሆኑ ተግባራት መጠነ ሰፊና የላቀ ውጤት የተመዘገበበት አርዓያነት ያለው እንቅስቃሴ ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እና ዓለም አቀፍ አጋሮችን ያሳተፈ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ሆኗል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ዛፍ በመትከል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ ሊለካ የሚችል እና ዘላቂ ከባቢያዊ ጥቅም የሚያስገኝ እንቅስቃሴ ነው። በተጨማሪም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስኬት ሀገራዊ ኩራትና ጽናት እንዲጎለብት በማድረግ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በመደመር ዕሳቤ ላይ በተመሰረተ የአፈጻጸም አቅም መፍታት እንደሚቻል አሳይቷል።

እ.ኤ.አ በ2027 የሚካሄደውን 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ሙሉ ተቀባይነት ማግኘቷ፣ በብራዚል ቤሌም በተካሄደው 30ኛው የኮፕ ጉባኤ ላይ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። ለዚህ ታሪካዊ ድል እና ክብር አንዱ መሠረት ደግሞ ሚሊዮኖችን ያሳተፈው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ነው።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች እንዲገነዘብ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የላቀ ውጤት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

ከ80 ሺህ በላይ እንግዶችን የሚያሳትፈው ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላትን ብርቱ አቅም ለዓለም የሚያሳይ ትልቅ ምዕራፍ ነው።

የኮፕ 32 ጉባኤን ማስተናገድ ለኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ከተቀዳጀችው ስኬት ባለፈ ስትራቴጂካዊ የሆኑ ሁለንተናዊ ጥቅሞችን ይዟል።

የዲፕሎማሲ ስኬት ቀዳሚው ነው፤ ሀገራችን ለዓመታት በአየር ንብረት ጉባኤዎች ላይ ስታነሳ የነበረውን የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ አጀንዳ በተግባር መምራት የምትችልበትን ዓለም አቀፍ መድረክ ይሰጣታል።

ጉባኤው በአዲስ አበባ መከናወኑ ከኢኮኖሚና ቱሪዝም አንጻርም ከፍ ያለ ፋይዳ አለው። የሀገር መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችና ሌሎችን ጨምሮ ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ገቢና የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

ከዚያ ባለፈም አዲስ አበባ በርካታ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ዋና ከተማ መሆኗን ለዓለም ማኅበረሰብ በተግባር የምታስመሰክርበትን ዕድል ይፈጥራል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥና ዘመናዊ መንገድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳየት ለገጽታ ግንባታም አስተዋጽኦ አለው።

በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስኬት እና የኮፕ 32 (COP 32) በኢትዮጵያ መካሄድ፣ ሀገራችን በአረንጓዴ አሻራ ዓለምን ማስደመሟን እና ለአየር ንብረት ጽናት ያላትን የማያወላውል ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው።

ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ በዘላቂ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያከናወነቻቸውን ተግባራት ለዓለም የምታስተዋውቅበት መድረክ በመሆኑ፣ ሀገራዊ ኩራታችንን ከፍ የሚያደርግ ነው።

‎#የመደመር_መንግሥት!

‎‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

‎‎#ባሕርዳር #ኅዳር_10_2019_ዓ_ም

‎‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous articleየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በራስ አቅም ሰፊ የማስፋፊያና ማሻሻያ ሥራ አከናወነ።
Next articleኢትዮጵያ ለኤሌክትሪፊኬሽን ትግበራ አጀንዳ የሰጠችው ድጋፍ የሚያስመሰግን ነው።