
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እና የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የጂኦፖለቲካውን ምኅዳር በመቀየር ለግብጽ ታሪካዊ እና የህልውና ስጋት ፈጥረዋል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ በዓባይ ወንዝ ላይ ብቸኛ የበላይነትን በመያዝ እና ቀይ ባሕርን እንደ የራሷ የደኅንነት ቀጣና በመቁጠር ላይ የተመሠረተ ነው።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሁለገብ ዕድገት እና ወደ ቀይ ባሕር የመመለስ ጥረት የግብጽን ይህን መዋቅራዊ የበላይነት ዕቅድ ውድቅ የሚያደርግ ነው።
የግብጽ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃቶች በጉራዕ እና ጉንደት ጦርነቶች እንደከሸፉት ሁሉ ዛሬም ወደ ዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ፍልሚያ በተቀየረው መድረክም ሽንፈቷ በየዘመኑ እየተደጋገመ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግድብን ገንብታ ወደ ኀይል ማመንጫነት ማሸጋገሯ ለግብጽ የታሪክ አዙሪት ትልቁ መሬት ላይ የወረደ ሽንፈት ነው።
ግብጽ ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ከባሕር በር አልባነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ርብርብ እንደ ቀጣናዊ የበላይነት ማጣት ስትመለከተው ይስተዋላል።
ይህ የግብጽ ስጋት ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የመነጨ እና በሌሎች ሀገራት ሉዓላዊ መብት ላይ ጣልቃ ለመግባት ያላት የናፍቆት ውጤት ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ የግብጽ ዋና ፍላጎት ኢትዮጵያ ብልጽግና እና ቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንዳይኖራት ማደናቀፍ ነው ይላሉ።
ለዚህም ሁሌም የማምታታት አካሄድን የምትከተለው ግብጽ ለዓባይ ውኃ ምንም አስተዋጽኦ ሳይኖራት በውኃ ትብብር ሂደት ላይ ተሳትፎ ብታደርግም መጨረሻዋ አለመፈረም እና ከስምምነት መውጣት እንደኾነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ከየትኛውም አካል ፍቃድ የምትጠብቅ ሳይኾን የሕዝቦቿን የልማት እና የደኅንነት ፍላጎት ለማሟላት በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በመከላከያ አቅም እና በቴክኖሎጂ እራሷን እያጠናከረች ጉዞዋን ቀጥላለች።
የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የኀይል እውነታውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዘነብልም አድርጎታል።
የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በጋራ የማልማት እና የጋራ የኢኮኖሚ ትስስር የመፍጠር አቅጣጫ ግብጽ ለዘመናት የዘረጋችውን የልዩነት እና የቁጥጥር ስልት አክሽፎታል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ጨምሮ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታደርገው ትስስር ጂኦፖለቲካዊ ክብደቷን እጅግ ከፍ አድርጎታል።
ግብጽ አጋሮቿን በማሠባሠብ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ግፊት በማድረግ እና በውስጥ ቀውሶች በመጫወት ኢትዮጵያን ለማደናቀፍ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በኢትዮጵያ ጽናት እና በቀጣናዊ ተቀባይነት ማጣት እየመከነ ነው።
ኢትዮጵያ የውስጥ ተግዳሮቶቿን እየተሻገረች፣ በሁሉም ዘርፍ ራሷን እያሳደገች እና የጂኦፖለቲካ አቋሟን እያጠናከረች ስትመጣ የግብጽ ታሪካዊ የበላይነት ፍላጎት እና ስጋት ወደ መክሸፍ እየተሸጋገረ መጥቷል።
የቀይ ባሕር መዳረሻ ጥያቄ እና የሕዳሴው ግድብ ስኬት የኢትዮጵያን ሁለገብ ትንሳኤ ከማረጋገጥ ባለፈ የምሥራቅ አፍሪካን የኀይል ስበት ማዕከል ወደ ባለቤቱ የሚመልስ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#AMECO #Red_Sea_Access #Abbay_River #Ethiopia_Sovereignty
#ባሕርዳር #ኅዳር_10_2019_ዓ_ም
✍️በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
