
በአማራ ክልል የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በክልሉ መንግሥት እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ አምስት ዘመናዊ የትራፊክ ኮምፕሌክሶች (በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በደብረ ብርሃን እና በደብረ ማርቆስ) አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን የክልሉ መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ አስታውቋል።
በክልሉ ስድስተኛ የኾነው እና በዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እየተገነባ የሚገኘው የእንጅባራ ትራፊክ ኮምፕሌክስ አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ መድረሱንም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ መምሪያ የሎጀስቲክስ ቡድን መሪ ማተቤ ተገኘ ለአሚኮ ገልጸዋል።
ግንቦት 2015 ዓ.ም በ4 ነጥብ 37 ሄክታር ቦታ ላይ የተጀመረው ይህ ግንባታ በ220 ሚሊዮን ብር በጀት ቢጀመርም በግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር ወጪው ወደ 400 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
በአሁኑ ወቅት የቢሮዎች፣ የአጥር፣ የጀነሬተር ቤት እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታዎች እየተጠናቀቁ ሲኾን በዝናብ ምክንያት ዘግይቶ የነበረውን የመለማመጃ ሜዳ እና መንገድ ሬንጅ የማልበስ ሥራ በማከናወን ኮምፕሌክሱን በዚህ ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ነው።
የእንጅባራ ትራፊክ ኮምፕሌክስ ሲጠናቀቅ የሚሰጣቸው ዋና ዋና አገልግሎቶችም፦
👉ለአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ለምዕራብ ጎጃም፣ ለሰሜን ጎጃም እና ለመተከል ዞኖች አገልግሎት ይሰጣል።
👉ከሰው ንክኪ እና ከሙስና የጸዳ፣ በዘመናዊ ካሜራ እና ቴክኖሎጂ የታገዘ የአሽከርካሪዎች ሥልጠና እና ምዘና በአንድ ማዕከል እንዲሰጥ ያደርጋል።
👉ብቁ አሽከርካሪዎችን በማፍራት የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል፤ የሰው ኀይል፣ ጊዜ እና ገንዘብንም ይቆጥባል።
👉ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
አቶ ማተቤ የክልሉ መንግሥት፣ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መሪዎች እና ኅብረተሰቡ ለግንባታው እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመሥግነው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_09_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
