
በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የየካቲት 23 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ 1ሺህ 559 ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ መርሐ ግብር ጀምሯል።
መርሐግብሩ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያግዝ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።
የተማሪ ወላጅ የኾኑት ወይዘሮ ይዳኙ አለባቸው በበኩላቸው ምገባው ቤተሰብ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ከመቀነስ ጀምሮ ለልጆች ውጤት መሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመኾኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በ2019 ዓ.ም 30 ሺህ ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ትበይን ባንቲሁን አስታውቀዋል።
እስካሁንም የየካቲት 23 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በስድስት ትምህርት ቤቶች 10 ሺህ 24 ተማሪዎች ተጠቃሚ እየኾኑ ነው።
ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የምገባ መርሐ ግብሮች መልካም ውጤት እንደታየባቸው ወይዘሮ ትበይን ጠቁመዋል። በምግብ እጥረት እና በችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ይርቁ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ዋስትና እንደኾነም ገልጸዋል።
የተማሪዎች ጤንነት፣ ትኩረት እና የአካዳሚክ ውጤት እያደገ እንዲመጣም አስችሏል ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የምገባው መጀመር የጉንፋን እና የድካም ስሜቶችን ከመቀነስ ባለፈ የምዝገባ ምጣኔን ከፍ አድርጓል።
ምገባው የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔም ከ15 በመቶ በላይ አሳድጓል ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ምክትል ርእሰ መምህር አማረ ጣማለው መርሐግብሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ወላጆች በቻሉት ሁሉ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከመንግሥት በጀት በተጨማሪም የማኅበረሰቡን መዋጮ በማቀናጀት የምገባ ሽፋኑን በማሳደግ ዕቅዱን ዕውን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን መምሪያው አስታውቋል።
ለአስተማማኝ ቀጣይነቱም የማኅበረሰቡ፣ የሕዝቡ እና የሌሎች አጋር አካላት ድጋፍ መጠናከር ይኖርበታል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#SchoolFeeding #StudentSuccess #BahirDar #Ameco #Ethiopia
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_09_2019_ዓ_ም
✍️በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
