
ዛሬ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ ተጽፏል።
ሠራዊቱ ከባሕላዊ የጦር መሣሪያ አስተሳሰብ እና ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ተላቅቆ ዘመኑ ያፈራቸውን እጅግ የላቁ እና የመጠቁ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የጠላትን የጥፋት ሕልም ገና ከሩቁ የሚያመክን ቁመና ላይ ይገኛል።
ስሙ ከሩቅ ሲጠራ የጠላት ሕልም ይመክናል፤ የጥፋት ድግስ የደገሱ ኀይሎችን ያርበደብዳል፤ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለምትሻው ኢትዮጵያ አስተማማኝ የሰላም ዋስትና፣ የሉዓላዊነት ጋሻ ነው፤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ አቅም ለማዳከም ተንኮል ለሚጎነጉኑ ኀይሎችም ብቸኛ መድኃኒት ነው።
ተቋሙ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ባከናወነው ጥልቅ እና ጠቅላላ ሪፎርም ውሥብሥብ ግዳጆችን በቅጽበት መፈጸም የሚችል ግዙፍ የባሕር፣ የየብስ፣ የኮማንዶ እና የአየር ወለድ ኀይሎችን ገንብቷል።
ከረጅም ርቀት ተወንጫፊ መድፎች እስከ ዘመናዊ ሚሳየሎች እና ታንኮች ድረስ በመታጠቅ የሜካናይዝድ አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጓል።
የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት በፈጠራና በምርምር በመታገዝ ከፍ ያለ ወታደራዊ አቅም ፈጥሯል።
እርሱን አትዳፈሩት ለሀገሩ ሉዓላዊነት መከበር አያንቀላፋምና፤ እርሱን አትገዳደሩት ለጠላት መድኃኒት ነውና፤ እርሱን አትተንኩሱት የሀገሪቱን የአየር ክልል እንዳይደፈር የሚያስችል የአየር ኀይል ገንብቷልና።
እርሱን አትሞግቱት አራተኛ እና አምስተኛ ትውልድ ተዋጊ ጄቶችን ታጥቋልና፤ እርሱን አክብሩት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የዘመኑ ሄሊኮፕተሮችን እንዲሁም ሰው አልባ ድሮኖችን በመታጠቅ የጠላትን እንቅስቃሴ ከሰማይ ኾኖ የሚቆጣጠር አስፈሪ ኀይል ገንብቷልና።
ዛሬ ላይ የሠራዊቱ አቅም ከሀገሩ ድንበር ተሻግሮ የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ማንኛውንም የስጋት ምንጭ ቀድሞ ለመለየት እና በቅጽበት ለማምከን የሚያስችል የተቀናጀ ክንድ ፈጥሯል።
የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ሠራዊቱ የደረሰበትን የብቃት ደረጃ አስመልክተው እንደገለጹት “ሠራዊቱ ከውስጥ እና ከውጭ የተሸረቡ አጥፊ ሴራዎችን እና የሽብር ዕቅዶችን በበሰለ ስትራቴጂያዊ አመራር፣ በላቀ ወታደራዊ ዲሲፕሊን፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በውጊያ ብቃት መክቶ በማክሸፍ የኢትዮጵያን አንድነት በአስተማማኝ ሁኔታ ጠብቋል”
በተካሄደው ጥልቅ ሪፎርም ተቋሙ በምድር፣ በአየር እና በሳይበር ምህዳሮች ያለው ሁለንተናዊ የውጊያ እና የደኅንነት አቅም በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ይህ አቅም የራሳችንን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ የአፍሪካን ቀንድ ሰላም ለማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ዝግጁነት ፈጥሯል።
በአጠቃላይ ሠራዊታችን የትላንት ታሪካችን አደራ ጠባቂ፣ የዛሬ ሰላማችን ዋስትና እና የነገ ብልጽግናችን መሠረትም ነው!
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር _ዳር #ኅዳር_09_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
