‎ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የወረርሽኝ መከላከያ ፈንድ ቦርድ በሊቀመንበርነት መመረጧ የአፍሪካን ድምጽ በዓለም መድረክ ለማሰማት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

15

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 25ኛው የፓንደሚክ ፈንድ ቦርድ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ቦርድ በጣምራ ሊቀመንበርነት እንድትመራ መመረጧ ተቀባይ ብቻ ሳትኾን ሀሳብ እና ዕቅድ አፍላቂ፣ እንዲሁም ፋይናንስን በማንቀሳቀስ ረገድ አህጉራዊ መሪነቷን ያረጋገጠችበት ነው ብለዋል።
‎
‎ከኮረና ወረርሽኝ በኋላ ወረርሽኞች ከመከሠታቸው በፊት ቀድሞ የመከላከል አቅምን ለመገንባት የተቋቋመው ይህ ቦርድ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ማካሄዱ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበችውን ተጨባጭ ለውጥ ለዓለም ለማሳየት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ሚኒስትሯ አስረድተዋል።
‎
‎በኮረና ወረርሽኝ ወቅት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የላብራቶሪ ምርመራ እና የዘረመል (DNA) ትንተና ውጤቶችን ወደ ውጭ ሀገር ልካ ትጠብቅ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር መቅደስ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው ርብርብ የራስን የጤና ሉዓላዊነት የማስከበር አቅም መገንባቱን ጠቁመዋል።
‎
‎ኢትዮጵያ ለወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅት እና ምላሽ አሠጣጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚለካው የጤና ደንብ መመዘኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ የ8 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ አፈጻጸሟን ከ62 በመቶ ወደ 70 በመቶ ማሳደግ መቻሏን ሚኒስትሯ ይፋ አድርገዋል።
‎
‎የኢትዮጵያን የወረርሽኝ መከላከል ሥራ ውጤታማ ያደረገው የሰው፣ የእንስሳት እና የአካባቢ ጤናን አቀናጅቶ የሚመራው የአንድ ጤና ፖሊሲ መኾኑን የገለጹት ዶክተር መቅደስ ይህም በጤና፣ በግብርና እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል የተፈጠረውን የመናበብ ባሕል ያሳየ መኾኑን አብራርተዋል።
‎
‎በዛሬው ዕለት ከ100 በላይ የሚኾኑ ዓለም አቀፍ እንግዶች በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚገኙትን የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ማሥተባበሪያ ማዕከል እና ዘመናዊ ላብራቶሪዎች መጎብኘታቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
‎
‎ጉባኤው በቀጣይ ሁለት ቀናት በሚያደርጋቸው ዝግ ውይይቶች በአፍሪካ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኞችን ለመከላከል አዳዲስ የፋይናንስ ድጋፎችን እንደሚያጸድቅ እና አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ተመላክቷል።
‎
‎#የመደመር_መንግሥት!
‎
‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
‎
‎#አዲስ_አበባ #ኅዳር_09_2019_ዓ_ም
‎
‎✍️ ዘጋቢ: ኢብራሂም መሃመድ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበቦረና የማኅበረሰቡን ሕይወት እንዲቀይሩ የተገነቡት 18 ሰው ሠራሽ ሐይቆች።
Next articleጤናማ ኅብረተሰብ የመፍጠር ጉዟችን በቀልጣፋ አገልግሎትና ዘመኑን በዋጀ ስርዓት መከናወን አለበት።